አዲስ አበባ፣ ግንቦት 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአፍሪካ ሕብረት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ለምለም ፍስሃ የሹመት ደብዳቤያቸውን ለሕብረቱ ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ አቀረቡ።
በዚህ ወቅት ሁለቱ ወገኖች በአህጉራዊ፣ ዓለም አቀፋዊ እና በሕብረቱ ቁልፍ ጉዳዮች ላይ መክረዋል።
በውይይቱ የሕብረቱ ኮሚሽን ሊቀ መንበር እንዳሉት፥ አምባሳደር ለምለም ያላቸው ልምድ እና የአመራር እውቀት በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ ሕብረት መካከል ያለውን ትብብር የበለጠ ያጠናክረዋል።
ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ሕብረት የምታደርገውን ቀጣይነት ያለው ድጋፍ አድንቀው፥ ኢትየጵያ ያካሄደችው ምርጫ ሰላማዊና ስርዓት ባለው መልኩ የተከናወነ መሆኑን አንስተዋል።
የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን የሕብረቱን ዓላማዎች ለመፈጸም እና ለአህጉራዊ ተግዳሮቶች ምላሽ ለመስጠት ከኢትዮጵያ ጋር በቅርበት እንደሚሰራም መግለጻቸውን ከሕብረቱ የተገኘው መረጃ አመላክቷል።
አምባሳደር ለምለም ፍስሃ በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረትን እና አህጉራዊ አጀንዳዎችን ለመደገፍ ያላትን ጠንካራ ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ከአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ጋር በትብብር ለመስራት ያለውን ዝግጁነትም አስረድተዋል።

