አዲስ አበባ፣ ግንቦት 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ምሕዳሩን ለማስፋት እያከናወነችው ያለው ሥራ የሚደነቅ ነው አሉ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ፡፡
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) ከአምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ ጋር የአሜሪካ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት በሚያደርጉበት ሁኔታ ላይ መክረዋል፡፡
ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) በዚህ ወቅት ÷ በኢትዮጵያ ስላሉት የኢንቨስትመንት ዕድሎች እና ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እየተሰሩ ስላሉ ሥራዎች ዙሪያ ገለጻ አድርገዋል፡፡
ባለሃብቶች የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች ለመፍታት እየተወሰዱ ስላሉ የፖሊሲ እና ተቋማዊ ማሻሻያዎች ላይም ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በኢትዮጵያና በአሜሪካ መካከል ያለው የኢንቨስትመንት ግንኙነት ይበልጥ መጠናከር አለበት ያሉት ኮሚሽነሩ÷ ከዚህ ጋር በተያያዘ በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል፡፡
የአሜሪካ-ኢትዮጵያ የንግድ ፎረምን በጋራ ለማዘጋጀት ከኤምባሲው ጋር በቅንጅት ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ በበኩላቸው ÷ በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ምህዳሩን ለማሻሻልና ዘርፎችን ለውጭ ባለሃብቶች ክፍት ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉትን የሪፎርም ሥራዎች አድንቀዋል፡፡
ማሻሻያዎቹ ይበልጥ በተጠናከረና በፈጠነ መልኩ መቀጠላቸው የአሜሪካ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ያለ ምንም ስጋት በስፋት ኢንቨስት ለማድረግ ምቹና ተስማሚ ሁኔታን እንደሚፈጥሩ ጠቁመዋል።
የአሜሪካ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ፣ በማዕድን፣ በጤና፣ በመሠረተ ልማትና በቴክኖሎጂ ዘርፎች ላይ ለመሰማራት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው ማረጋገጣቸውንም ኮሚሽኑ ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡

