አዲስ አበባ፣ ግንቦት 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ 8ኛውን የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግሥት አገልግሎት ስራ አስጀምረዋል።
ከንቲባዋ በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት÷ 7ኛውን ዙር ምርጫ ባጠናቀቅንበት ማግስት ዛሬ 8ኛውን የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግሥት አገልግሎት ክፍት አድርገናል ብለዋል።
ለሕዝባችን በገባነው ቃል መሰረት ዛሬ በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ባለ 7 ወለል ህንፃ ገንብተን በቴክኖሎጂ ተደራጅቶ 96 ተገልጋዮችን በአንድ ጊዜ የሚያስተናግዱ መስኮቶች ያሉት በ22 ተቋማትና በ114 አገልግሎቶች ስራ አስጀምረናል ነው ያሉት።
ማዕከሉ ከፍ ባለ ጥራት እጅግ ውብ፣ ፅዱ፣ አካታች የሆነ ለአካል ጉዳተኞች ምቹ፣ የህፃናት ማቆያ ያለው፣ ለሰራተኞችም ለተገልጋዮችም ምቹ ሆኖ የተገነባ መሆኑን ገልጸዋል።
በቀጣይም በርካታ አገልግሎቶችን ወደ መሶብ ማዕከል በማስገባት ነዋሪዎች ቀልጣፋና ፍትሃዊ አገልግሎት እንዲያገኙ እናደርጋለን ብለዋል።
የከተማዋ ነዋሪዎች መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግሥት አገልግሎት ለዘመናት አሰልቺ ከነበረውና ውጣ ውረድ ከበዛበት እና በእጅ መንሻ ከተማረራችሁበት ቢሮክራሲ የሚያላቅቃችሁ በመሆኑ እንኳን ደስ አላችሁም ነው ያሉት።
በማዕከላቱ በቦታ ሳትገደቡ በሚቀርባችሁ በየትኛውም ማዕከል በመገኘት ተገልገሉ ሲሉም አስገንዝበዋል።
ማዕከሉ ተጠናቅቆ ስራ እንዲጀምር ትብብር ላደረጉ አካላት በሙሉ ምስጋና አቅርበዋል።

