አዲስ አበባ፣ ግንቦት 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ከሩሲያ አቻቸው ጋር ፊት ለፊት ለመወያየት ሀሳብ አቅርበዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ለሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በፃፉት ደብዳቤ ሰላም ሊመጣ የሚችለው በሁለቱ ሀገራት መካከል ቀጥተኛ ውይይት ማድረግ ሲቻል መሆኑን ገልጸዋል።
ጦርነቱ አሁንም የአሜሪካ እና የምዕራባውያን የትኩረት አቅጣጫ ሊሆን አይገባም ያሉት ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ÷ ሙሉ በሙሉ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጠይቀዋል፡፡
ክሬምሊን በበኩሉ ከፕሬዚዳንት ዘለንስኪ የተላከውን ደብዳቤ መቀበሉን ያረጋገጠ ሲሆን÷ በጉዳዩ ላይ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ማብራሪያ እንደሚሰጡ አስታውቋል፡፡
ዘለንስኪ የእንደራደር ጥያቄ ሲያቀርቡ የመጀመሪያቸው እንዳልሆነ ያስታወሰው ክሬምሊን÷ ቁርጠኛ ንግግር ማድረግ ከፈለጉ ሞስኮ መጥተው ፕሬዚዳንት ፑቲንን ማነጋገር ይችላሉ ሲል መግለጹን ቢቢሲ ዘግቧል።
የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በትላንትናው ዕለት ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት÷ ጦርነቱን ለማስቆም የሩሲያ እና ዩክሬን መሪዎች ፊት ለፊት መገናኘት ወሳኝ ነው።
ፕሬዚዳንት ፑቲን ሩሲያ በወታደራዊ ዘመቻ በተቆጣጠረቻቸው ዶነስክ፣ ሉሃነስክ፣ ኬርሰን እና ዛፖሮዥያ ግዛቶች ዩክሬን የምታደርገውን ጥቃት በማቆም ጦሯን እንድታስወጣ እና ኔቶን ለመቀላቀል የምታደርገውን ጥረት እንድታቆም ሲጠይቁ ቆይተዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ በበኩላቸው÷ እነዚህን ግዛቶች እንደ ክሬሚያ ሁሉ በሃይል ማስወሰድ እንደማይፈልጉ ገልጸዋል።
ግዛቶቹ ወደ ሩሲያ ከተካለሉ በሌላ ጊዜ ሞስኮ ኬቭን እንድትወር ፈቃድ መስጠት ነው ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል።
ከዚህ ቀደም ሁለቱ ሀገራትን በሦስተኛ ወገን አደራዳሪዎች ለማሸማገል በጄኔቫ፣ አቡ ዳቢ እና ኢስታንቡል የተደረጉ ድርድሮች ያለስኬት መጠናቀቃቸው ይታወቃል።
ሚኪያስ አየለ

