Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ምርጫው አካል ጉዳተኞች ከመቼውም ጊዜ የላቀ ተሳትፎ ያደረጉበት ነው – ፌዴሬሽኑ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ አካል ጉዳተኞች ከመቼውም ጊዜ በላቀ ደረጃ ተሳትፎ ያደረጉበት ነው አለ።
ፌዴሬሽኑ ምርጫውን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ እንዳለው ከአባል ማህበራት ጋር በመተባበር የአካል ጉዳተኞችን ተሳትፎና የተደራሽነት ሁኔታ በቅርበት ሲታዘብ ቆይቷል፡፡
በዚህም በምርጫው 275 አካል ጉዳተኞች በዕጩነት መቅረባቸውንና ይህም በ6ኛው አጠቃላይ ምርጫ ከነበረው 99 የዕጩዎች ቁጥር አንጻር ሲታይ ከፍተኛ መሻሻል የታየበት ነው ብሏል።
165 ሺህ የሚገመቱ አካል ጉዳተኞች በመራጭነት መመዝገባቸውን የገለጸው ፌዴሬሽኑ አጠቃላይ የምርጫ ሂደቱ ሰላማዊ እንዲሁም ደንቦችንና መመሪያዎችን የተከተለ እንደነበር አንስቷል፡፡
ፌዴሬሽኑ በመግለጫው የምርጫ አስፈጻሚዎች ለአካል ጉዳተኞች ከወትሮው የተሻለ ሁኔታዎችን የማመቻቸትና ቅድሚያ የመስጠት ሥራዎችን አከናውነዋል ነው ያለው።
በቀጣይም አካል ጉዳተኞች ፖለቲካዊ መብቶቻቸውን ሙሉ በሙሉ እንዲጠቀሙ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል በመግለጽ ለምርጫ ቦርድና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ምስጋና አቅርቧል።
Exit mobile version