Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ባህር ዳርና ሃዋሳ ዩኒቨርሲቲዎች በተለያየ መርሃ ግብር ያሰለጠኗቸውን 12 ሺህ 300 ተማሪዎች አስመረቁ

አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 23 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ባህር ዳር እና ሃዋሳ ዩኒቨርሲቲዎች በተለያየ መርሃ ግብር ያሰለጠኗቸውን 12 ሺህ 300 ተማሪዎች በዛሬው እለት አስመረቁ፡፡

ከዚህ ውስጥ ሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ 4 ሺህ 780 ተማሪዎችን በተለያዩ መርሃ ግብሮች አስመርቋል፡፡

ተማሪዎቹ ከአንደኛ ዲግሪ እስከ ፒ ኤች ዲ ድረስ በተለያዩ የሙያ መስኮች የሰለጠኑ ሲሆን የምረቃ ስነ ስርአቱም በቪዲዮ ኮንፈረንስ ተካሂዷል፡፡

የዩኒቨሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር አያኖ በራሶ ለተመራቂዎቹ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በሃገር እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ለተከሰተው ፈተና የመፍትሄ አካል ለመሆን ሃገራዊ አንድነታችሁን እና ወንድማማችነታችሁን አስጠብቃችሁ ልትቀጥሉ ይገባል ብለዋል በመልዕክታቸው፡፡

ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ደግሞ በተለያዩ የሙያ መስኮች ያሰለጠናቸውን 7 ሺህ 520 ተማሪዎችን አስመርቋል፡፡

የምረቃ ሥነ ስርዓቱ ጥቂት ተማሪዎችን ፊት ለፊትና አብዛኛዎቹን ባሉበት በተለያዩ አማራጮች በቀጥታ ስርጭት በመታገዝ ተከናውኗል፡፡

ተመራቂዎቹ በህክምናና ጤና ሳይንስ፣ በስነ-ህንጻ እና በአውቶሞቲቭ ምህንድስና በመደበኛውና በሌሎች ተከታታይ መርሀ ግብሮች የሰለጠኑ 4 ሺህ 543 ተማሪዎች ናቸው፡፡

በድኅረ መርቃ መርሀ ግብር በሁለተኛ ዲግሪ በመደበኛውና በተከታታይ መርሀ ግብር ደግሞ 2 ሺህ 254 ተማሪዎች፣ በሦስተኛ ዲግሪ መርሀ ግብር 40 ተማሪዎች፣ እንዲሁም በስፔሻሊቲ መርሀ ግብር 41 ተማሪዎች፣ በሰርቲፊኬት መርሀ ግብር 642 ተማሪዎች በድምሩ 7 ሺህ 520 ተማሪዎችን በበይነ መረብ በመታገዝ አስመርቋል፡፡

በይስማው አደራው፤ ተጨማሪ መረጃ ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ

Exit mobile version