አዲስ አበባ፣ ግንቦት 30 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ዘላቂ እና የማይበገር ኢኮኖሚ በመገንባት ሂደት መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት ያስፈልጋል።
ኢትዮጵያ በግብርና ዘርፍ ብቻ ተወስኖ የነበረውን የኢኮኖሚ መሰረት በማስፋት ብዝሃ ዘርፍ የኢኮኖሚ ስርዓትን መተግበር ጀምራለች።
የብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚ ስርዓት ለሁሉም ዘርፎች ተገቢውን ትኩረት በመስጠት ባለፉት ዓመታት በተሰሩ ስራዎች ከፍተኛ ስኬት ማስመዝገብ ተችሏል።
ኢትዮጵያ በተለይም ሰፊ የግብርና፣ የሰው ኃይል እንዲሁም ጠንካራ የታዳሽ ኃይል መሰረት ያላት መሆኑ ወደ ብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚ ለምታደርገው ሽግግር ጉልህ ሚና ይጫወታል፡፡
ይህንን በመገንዘብ በግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ቱሪዝም፣ ማዕድንና ቴክኖሎጂ ዘርፎች ተግባራዊ በተደረጉ የብዝሃ ዘርፍ የኢኮኖሚ ስርዓት አመርቂ ውጤት እየተመዘገበ ይገኛል፡፡
ቀደም ሲል በግብርና ላይ ብቻ የተወሰነውን የኢኮኖሚ ስርዓት በማስፋት በቱሪዝም፣ በኢነርጂ፣ በአገልግሎትና አምራች ዘርፎች በተከናወኑ ሰፋፊ ስራዎች አበረታች እመርታ ተመዝግቧል፡፡
ለአብነትም በመላ ሀገሪቱ የተከናወኑ የቱሪዝም መዳረሻዎችን የማስፋት ስራዎች ይጠቀሳሉ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት ገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለሀገር እና ገበታ ለትውልድ የመሳሰሉ መርሐ ግብሮች ተተግብረው የቱሪዝሙ አቅም ከፍተኛ መሆኑን ማሳየት ተችሏል።
ከዚህ በተጨማሪ ነባር የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማዘመንና አዳዲስ መዳረሻዎችን በመገንባት የቱሪዝም ዘርፉ ያለውን የኢኮኖሚ ድርሻ ያሳደገ ውጤትና ተስፋ ተገኝቷል።
በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ በተለይም በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አማካኝነት የውጭ ምንዛሪን ማስቀረት የሚችሉ ተኪ ምርቶች ላይ ትኩረት በማድረግ ተጨባጭ ውጤት ተመዝግቧል፡፡
ከ47 በመቶ ያልተሻገረውን የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም ባለፉት ሦስት ዓመታት ብቻ ወደ 66 ነጥብ 3 በመቶ ማሳደግ ተችሏል፡፡
በተመሳሳይ በማዕድን ዘርፍ ከፍተኛ ስኬት የተመዘገበ ሲሆን፥ የወርቅ፣ የብረት፣ የከበሩ ማዕድናት እንዲሁም የሲምንቶ ምርት መጠን በእጅጉ ጨምሯል፡፡
የልማት ስራዎች በቴክኖሎጂ ታግዘው በሚፈለገው ፍጥነት እድገትን እንዲያረጋግጡ ባለፉት ዓመታት የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማትን በማስፋፋት ረገድ በርካታ ተግባራት የተከናወኑ ሲሆን፤ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዘርፍ አስደናቂ ውጤት መጥቷል።
በዚህም አገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን የአገልግሎት ተደራሽነትን ከማስፋት ባሻገር የኅብረተሰቡን የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት ማሻሻል ተችሏል።
የሞባይል ተጠቃሚዎች ቁጥር ከ97 ሚሊየን መሻገሩ ዲጂታል የፋይናንስ እንቅስቃሴን በማጎልበት በኩል የራሱን ሚና እያበረከተ ነው።

