አዲስ አበባ፣ ሰኔ 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ) በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ከሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ቡድኖች ጋር ግንኙነት የለኝም አለ፡፡
ኦብነግ ባወጣው መግለጫ በሰላማዊ የፖለቲካ መንገድ እንደሚንቀሳቀስ በመግለጽ፥ ቀደም ሲል ከመንግስት ጋር የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ለማስፈጸም ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጧል፡፡
ስምምነቱ ከተተገበረበት ጊዜ ጀምሮ በሶማሌ ክልል ሰላም መስፈኑን የገለጸው ኦብነግ፥ ይህም የስምምነቱን አስፈላጊነትና ሁሉም ወገኖች ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ያላቸውን ቁርጠኝነት ያሳያል ብሏል።
የግል ፍላጎታቸውን ማሳካት ያቃታቸው ጥቂት ግለሰቦች በክልሉ የተገኘውን ሰላም፣ መረጋጋትና ልማት የሚያናጋ ግጭት ለመቀስቀስ የድርጅቱን ስም ያለፍቃድ በመጠቀም የሚያደርጉትን ሙከራ በጽኑ አውግዟል፡፡
መሰል ድርጊቶች ከድርጅቱ መርሆዎች ጋር የሚጣረሱና በክልሉ በብዙ ልፋት የመጣውን ሰላምና መረጋጋት አደጋ ላይ የሚጥሉ እንቅስቃሴዎችን እንደሚታገል አረጋግጧል፡፡
መንግሥትን ለመጣል ከሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ኃይሎች ጋር ምንም ዓይነት ጥምረት አለመመስረቱን ጠቅሶ፥ በሰላማዊና በዲሞክራሲያዊ መንገድ ለመታገል ቁርጠኛ መሆኑን አሳውቋል፡፡
የቀድሞው የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ አብዲራህማን ማህዲ በአሁኑ ወቅት በኦብነግ ውስጥ ምንም ዓይነት የአመራር ቦታ እንደሌላቸው ፓርቲው በመግለጫው አመልክቷል፡፡
ግለሰቡ በኦብነግ ስም የሚሰጧቸው መግለጫዎች የፓርቲውን ይፋዊ አቋም የማይወክሉ መሆናቸውን ገልጿል፡፡

