አዲስ አበባ፣ ሰኔ 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በዘንድሮው ክረምት 2 ነጥብ 4 ሚሊየን ወጣቶችን በበጎ ፈቃድ ሥራ ለማሳተፍ ዝግጅት እየተደረገ ነው አለ የክልሉ የወጣቶች ጉዳይና በጎ ፈቃድ አገልግሎት ኮሚሽን።
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ማርቆስ ማቲዮስ እንዳሉት ÷ የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት የሕብረተሰቡን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ከመፍታት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው፡፡
በዘንድሮው ክረምትም ወጣቶችን በተለያዩ የበጎ ፈቃድ ዘርፎች በንቃት በማሳተፍ የሕብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
የወጣቶችን ስብዕና በመገንባት እና የበጎ ፈቃድ ባሕልን በማጎልበት የአንድነትና የአብሮነት እሴቶችን ለማጠናከር ትኩረት እንደሚሰጥ አመልክተዋል፡፡
በበጋ ወራት በተመዘገቡ ስኬቶች ላይ በመመስረት በክረምት ወራትም ተመሳሳይ ውጤቶችን ለማስመዝገብ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በትብብር እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በዘንድሮው የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ መርሐ ግብር ከ6 ነጥብ 6 ሚሊየን በላይ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እንደታቀደ መጥቀሳቸውንም የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡

