አዲስ አበባ፣ ሰኔ 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በባዮ ቴክኖሎጂ ምርምር “ኢቲቱ” የተሰኘና ወተትን ለማርጋት የሚያስችል የፕሮ ባዮቲክ እርሾ ይፋ አድርጓል።
ኢንስቲትዩቱ አዲሱን የምርምር ውጤት ይፋ ያደረገው የዓለም የወተት ቀንን አስመልክቶ ዛሬ በተዘጋጀ የጋራ የውይይት መድረክ እና ዓውደ ርዕይ ላይ ነው።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ንጉሴ ደቻሳ (ፕ/ር) በዚህ ወቅት ÷ “ኢቲቱ” የተሰኘው አዲሱ የፕሮ ባዮቲክ እርሾ በሀገሪቱ ያሉ የወተት ማቀነባበሪያ ድርጅቶች በውጭ ምንዛሪ ከውጭ አስገብተው የሚጠቀሙበትን እርሾ የሚተካ ነው ብለዋል።
ይህ የምርምር ውጤት የወተት ማቀነባበሪያዎችን የውጪ ምንዛሪ ከማዳን ባለፈ ፓስቸራይዝድ የተደረገ ወተትን በአራት ሰዓታት ውስጥ ማርጋት እንደሚያስችል ጠቁመዋል።
ኢንስቲትዩቱ ምርምር ከሚያደርግባቸው የግብርና ውጤቶች ውስጥ ወተትና የወተት ተዋጽኦዎች ዋነኞቹ መሆናቸውን ገልጸው÷ ምርቱ ለምግብ ዋስትና እና ለጤንነት ወሳኝ የሆኑ ንጥረ ነገሮችን የያዘ መሆኑን አብራርተዋል።
ኢንስቲትዩቱ የተሻሻሉ የሰብል እና የእንስሳት ዝርያዎችን በምርምር በማውጣት ለዘርፉ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ መጥቀሳቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በአሁኑ ወቅትም በወተት ምርታማነት ላይ ትኩረት ያደረጉ በባዮ ቴክኖሎጂ የታገዙ ልዩ ልዩ ምርምሮች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ነው የገለጹት፡፡

