አዲስ አበባ፣ ሰኔ 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስና ዲጂታል ቴክኖሎጂ ዕውቀትን ለትውልድ የማሻገሩን ሥራ አጠናክሮ ይቀጥላል አሉ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር)::
18ኛው ዓመታዊ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጻሕፍት ዓውደ ርዕይ ስድስት ኪሎ በሚገኘው በዩኒቨርሲቲው ዋና ግቢ በይፋ ተከፍቷል።
ዓውደ ርዕዩ ከሰኔ 1 ቀን እስከ ሰኔ 7 ቀን 2018 ዓ.ም የሚካሄድ ሲሆን÷ ከ40 በላይ የመጻሕፍት አከፋፋዮች፣ አሳታሚዎችና የመጻሕፍት መደብሮች ተሳትፈዋል፡፡
በመጻሕፍት ዓውደ ርዕዩ በሁሉም የዕውቀት ዘርፎች ላይ የሚያተኩሩ በርካታ ነባርና አዳዲስ መጻሕፍት ለአንባቢያን በቅናሽ ዋጋ ቀርበዋል፡፡
አዳዲስ መጻሕፍት ይመረቃሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም የዩኒቨርሲቲው መረጃ ያመላክታል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ ላለፉት ከ50 ዓመታት በላይ በርካታ መጻሕፍትን ሲያሳትምና ተደራሽ ሲያደርግ ቆይቷል።
ዩኒቨርሲቲው ወደ ራስ ገዝነት በሚያደርገው ጉዞም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስን አቅም የማሳደግና የዘመኑን ገበያ በመጠቀም ተደራሽነቱን የሚያሰፉ ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።
በቀጣይ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስና ዲጂታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም ዕውቀትን ለትውልድ የማሻገርና ተቋሙ ከሌሎች መሰል ተቋማት ጋር ያለውን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ እንደሚሠራም አረጋግጠዋል፡፡

