Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በኦሮሚያ ክልል 29 ሚሊየን ኩንታል ፍራፍሬ ምርት ተገኘ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል ለፍራፍሬ ልማት ያለውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም በ2018 በጀት ዓመት 29 ሚሊየን ኩንታል የፍራፍሬ ምርት ተመርቷል አለ የክልሉ ግብርና ቢሮ።

በቢሮው የፍራፍሬ ልማት ዳይሬክተር ቻላቸው አዱኛ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት ÷በክልሉ የፍራፍሬ ምርት ውጤታማነትን ለማጠናከር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡

ክልሉ ለፍራፍሬ ልማት ምቹ የአየር ንብረት፣ በቂ የዝናብ መጠንና ተስማሚ የአፈር ዓይነት ያለው በመሆኑ ለዘርፉ ምርታማነት ከፍተኛ አቅም እንዳለው አውስተዋል፡፡

በተለይም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የምግብ ሥርዓትን ከማሻሻል ረገድ ሚናው የላቀ በመሆኑ በተከወኑ በርካታ ተግባራት ውጤት መመዝገቡን አመልክተዋል፡፡

እንደ አቮካዶ፣ ፓፓያ፣ ሙዝ፣ ማንጎ፣ ብርቱካን፣ አፕል እና ሎሚ ያሉ ዋና ዋና የፍራፍሬ ዓይነቶች የዞኖቹን መልክዓ ምድርና የአየር ንብረት መሰረት በማድረግ እየለሙ ይገኛሉ ነው ያሉት፡፡

ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ የተሻሻሉ የፍራፍሬ ምርጥ ዘሮችን በመጠቀምና የማስፈጸም አቅምን በማሻሻል ልማቱ እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።

በዚህም በ2013 ዓ.ም ከ90 ሺህ ሄክታር ያልበለጠውን የፍራፍሬ ልማት በአሁኑ ወቅት በ240 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ እየለማ መሆኑን ተናግረዋል።

ክልሉ ለፍራፍሬ ልማት ያለውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም በበጀት ዓመቱ 29 ሚሊየን ኩንታል ፍራፍሬ መመረቱን ጠቁመዋል።

ከዚህ ውስጥም ከ 8 ሚሊየን ኩንታል በላይ የሚሆነው የአቮካዶ ምርት መሆኑን ነው አቶ ቻላቸው የተናገሩት፡፡

ባለፈው ዓመት 2 ሺህ 400 ኩንታል የአቮካዶ ምርት ወደ ውጭ መላኩን አንስተው፥ ዘንድሮም በተሻለ ሁኔታ ለመላክ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

በዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የአትክልትና ፍራፍሬ ችግኞችን በስፋት ለመትከል አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝም አመልክተዋል፡፡

በአቤል ነዋይ

Exit mobile version