አዲስ አበባ፣ ሰኔ 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በቻይና እና ሰሜን ኮሪያ መካከል ያለው ግንኙነት ወደ አዲስ የእድገትና የትብብር ምዕራፍ ተሸጋግሯል አሉ የቻይና ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ።
ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ ከሰባት ዓመታት በኋላ ዛሬ ወደ ሰሜን ኮሪያ ያቀኑ ሲሆን÷ በፒዮንግያንግም በሀገሪቱ መሪ ኪም ጆንግ ኡን የእንኳን ደህና መጡ ግብዣ ተደርጎላቸዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ሺ በዚህ ወቅት ባደረጉት ንግግር÷ የሁለቱ ሀገራትን ስልታዊ ግንኙነት ለማጠናከር ያላቸውን ዝግጁነት ገልጸዋል።
ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣውን የሀገራቱን ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር የሀገራቱን ሕዝቦች የበለጠ ተጠቃሚ ለማድረግ፣ ለቀጣናውና ለዓለም ሰላም፣ ለልማት እና ብልጽግና አዎንታዊ አስተዋጽዖ ያደርጋል ብለዋል።
ሁለቱ ሀገራት የጋራ ፖለቲካዊ መተማመን መሰረትን ማጠናከር እና የተግባራዊ ትብብር ደረጃን ማሳደግ እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
ቻይና እና ሰሜን ኮሪያ የሶሻሊስት ሀገራት መሆናቸውን ያስታወሱት ሺ ጂንፒንግ÷ በመካከላቸው ያለውን ወዳጅነት በጋራ አመለካከታቸው እና እምነታቸው እንዲሁም በጋራ ግባቸው ላይ የተመሰረተ እና በጥልቅ ታሪካዊ ትስስር የተደገፈ፤ ጠንካራ የፖለቲካ መሰረት ያለው መሆኑን አንስተዋል።
ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ ወዳጅነት፣ የጋራ የወደፊት ዓላማ እና መደጋገፍ የሀገራቱ ግንኙነት መገለጫዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በአጠቃላይ ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ በቻይና እና ሰሜን ኮሪያ ግንኙነት ላይ አራት ሐሳቦችን አጽንኦት ሰጥተው አንስተዋል።
ሁለቱ ወገኖች በከፍተኛ ደረጃ ያሉ የመሪዎች ጉብኝት፣ ውይይት እና መሰል ልውውጦችን መቀጠል እንዲሁም የፖለቲካ መተማመኛ መሰረታቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው በቀዳሚነት አሳስበዋል።
በሁለተኛ ደረጃ የሕዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እና ተግባራዊ ትብብርን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አስታውቀዋል።
በቻይና እና ሰሜን ኮሪያ መካከል ያለውን ትብብር እንደ ጉልበት በመጠቀም በሕዝብ መካከል ያለውን ትስስር ማጠናከር ሌላው የሀገራቱ የግንኙነት ማጠንጠኛ እንደሆነ አስረድተዋል።
በመጨረሻም ፍትሐዊነትን የሁለቱ ሀገራት የስትራቴጂካዊ ግንኙነት መርህ አድርጎ ማቆየት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በብርሃኑ አበራ

