Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የመዲናዋ 3ኛው ዙር የኮሪደር ልማት ሥራ በጥራትና ፍጥነት እየተከናወነ ነው – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሶስተኛው ዙር የኮሪደር ልማት ሥራ በጥራት እና ፍጥነት እየተከናወነ ነው አሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፡፡

ከንቲባዋ በዛሬው ዕለት በሶስተኛ ዙር የተጀመሩ 13 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር የሚሸፍኑ የኮሪደር ልማት ሥራዎችን ተዘዋውረው ገምግመዋል፡፡

በዚህ ወቅትም የኮሪደር ልማት ሥራዎቹ በአምስት የኮሪደር መስመሮች ተከፋፍለው እየተከናወኑ እንደሚገኙ አመልክተዋል፡፡

በዚህም መሰረት፡-

👉 ከቦሌ መድሃኔዓለም እስከ ጎላጎል (የቦሌ አትላስን መንገድ ከመስቀል አደባባይ መገናኛ መንገድ ጋር የሚገናኝ)፤

👉 ከጎላጎል እስከ እንግሊዝ (የቀበና መገናኛ መንገድን ከመስቀል አደባባይ መገናኛ መንገድ ጋር የሚገናኝ)፤

👉 ከቦሌ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት በሞኤኮ እስከ ቦሌ መገናኛ መንገድ (የቦሌ አትላስን መንገድ ከቦሌ መገናኛ መንገድ ጋር የሚገናኝ)፤

👉 ከኢምፔሪያል በአደይ አበባ ስታዲየምም እስከ ሻላ መናፈሻ፤

👉 ከውሃ ልማት በአትላስ ያለውን እና ከአትላስ እስከ ቦሌ ሩዋንዳ (የቦሌ አትላስ መንገድን ከመስቀል አደባባይ መገናኛ መንገድ ጋር የሚገናኙ) ናቸው፡፡

ከንቲባ አዳነች የኮሪደር ልማት ሥራዎቹ ሰፋፊ የእግረኛ መንገድ፣ የሳይክል መንገድ እና ለትራንስፖርት አገልግሎት ምቹ እንዲሆኑ ተደርገው እየተገነቡ ነው ብለዋል፡፡

በተጨማሪም በርካታ የሕዝብ አገልግሎት መስጫ ግንባታዎችን የያዙ ሲሆን÷ የግንባታ ሒደቱም በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

በአደይ አበባ ስታዲየም ዙሪያ አስቀድመው የተጀመሩ የኮሪደርና ሌሎች መሠረተ ልማት ግንባታዎች በፍጥነትና በጥራት እንዲከናወኑ የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል ነው ያሉት።

ከኮሪደሩ በተጨማሪም ለብዙ ዘመናት ተረስቶ የኖረ፣ ከሕዝብ ተወስዶ በግለሰቦች ያለአግባብ ተወሮ ለብዙ ብልሽት ተዳርጎ የኖረውን ቦታ ለሕዝብ አገልግሎት እንዲውል ተደርጎ በመሰራት ላይ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡

ፕሮጀክቶቹን እስከ ሰኔ ወር መጨረሻ ሙሉ በሙሉ አጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

Exit mobile version