አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 23፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) አዲስ አበባ የበጎ ፍቃድ ማዕከል እንድትሆን ወጣቶች፣ የኪነጥበብና የስፖርቱ ማህበረሰብ የሚያደርጉት ተሳትፎ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ገለፁ።
ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እና በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግስት የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ጃንጥራር አባይ ከኪነጥበብ ባለሙያዎች፣ ከስፖርት ማህበረሰብ አባላት እና ከመገናኛ ብዙኃን አመራሮች ጋር ውይይት አካሂደዋል።
በውይይቱ ላይም ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ፥ በመጠናቀቅ ላይ በሚገኘው 2012 ዓ.ም ወጣቶች፣ የኪነጥበብ ባለሙያዎች፣ የስፖርቱ ማህበረሰብ እና መላው ነዋሪ ከተማችን እንደ ስሟ አዲስ እና አበባ እንድትሆን ዘርፈ ብዙ ጥረት አድርገዋል ብለዋል።
ለዚህ በጎ ተግባር ተሳታፊ ለሆኑ አካላት እና መላው የከተማው ነዋሪዎች የከተማ አስተዳደሩ ትልቅ ክብር እንዳለውም ተናግረዋል።
በክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የአቅመ ደካሞችን ቤት ከማደስ ጀምሮ የአረንጓዴ አሻራ ተሳትፎ፣ ኮቪድ19 ወረርሽኝ በመከላከል እና ድጋፍ በማሰባሰብ እንዲሁም ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ድጋፍ የተደረገው ስራ ለሁሉም አርዓያ መሆን የሚችሉ ሲሆን፥ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ሲሉም ገልፀዋል።
ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች፥ “መጪውን አዲስ አመት ስንቀበልም በአብሮነት መንፈስ በጋራ በመሆን በይቅርታ ፣በብሩህ ተስፋ ብስራት ሊሆን ይገባል ብለዋል።
ለዚህም የከተማዋ ወጣቶች፣ የስፖርት ቤተሰቡ፣ የሚዲያ ባለሞያዎች እና የኪነ-ጥበብ ባለሞያዎች ንቁ ተሳትፎ ሊያደርጉ ይገባል ማለታቸውንም ከአዲስ አበባ ፕሬስ ሰክረተሪያት ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

