Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የባህር በርና ሉዓላዊነት

የባህር በር የአንድን ሀገር ሉዓላዊነት ሙሉ ያደርገዋል፡፡ በተለይ የበለጸገ ኢኮኖሚ ካላቸው ሀገራት ጫና እና ጥገኝነት ለመውጣት ለሚታገሉ እና የባህር በር ቅርባቸው ለሆኑ ሀገራት ወደብ የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ ገቢና ወጪ ንግድን በነጻነት ለማከናወን የባህር በር ሙሉ ነጻነትን ያጎናጽፋልና፡፡

የባህር በር በቅርባቸው እያለ የቅርብ ሩቅ የሆነባቸው ሀገራት ለጂኦፖለቲካዊ ተጽዕኖ ተጋላጭ ናቸው፡፡

ቀድሞ ላልተዘጋጀ ሀገር፣ ከባህር ማዶ፣ ባህር ላይ እና ከባህር ወዲህ የሚዶለትበትን ሴራ ለመቀልበስ ቀላል አይሆንለትም፡፡ ስለዚህ የባህር በር ጉዳይ ቀጥታ ከሀገራዊ ደህንነት ጋርም የሚገናኝ ጉዳይ ነው፡፡

እንደ ኢትዮጵያ ላሉ የባህር በራቸውን በግፍ ለተነጠቁ ሀገራት፣ የባህር በርን ማጣት በሉዓላዊነታቸው ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራል።

ወደብ የሌላቸው ሀገራት ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ ለመላክና ለማስገባት በጎረቤት ሀገራት ወደቦች ላይ ጥገኛ ናቸው። ይህ ጥገኝነት በወደብ ኪራይ እና በታሪፍ ምክንያት የኢኮኖሚ ሉዓላዊነታቸውን ይጎዳል።

አይበለውና ከጎረቤት ሀገራት ጋር አለመግባባት በሚፈጠርበት ጊዜ የወደብ አገልግሎት ሊከለከል ወይም ሊደናቀፍ ይችላል። ይህም የሀገርን ህልውና እና የውስጥ ደህንነት አደጋ ላይ ይጥላል።

ወደብን በሊዝ ኪራይ የሚሰጥ ሀገር ከኪራይ፣ ከታሪፍ እና ከትራንዚት አገልግሎት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እና የገቢ ምንጭ ያገኛል፡፡

ነገር ግን ወደብን በሊዝ (በኪራይ) የሚወስደው ሀገር መሬቱ የሌላ ሀገር ግዛት በመሆኑ፣ ወደብ ባለበት ሀገር ያለመረጋጋት ቢፈጠር የተከራይ ሀገር ተጠቃሚነት አደጋ ላይ ይወድቃል፡፡

የባህር በር የሌላቸው ሀገራት በዓለም አቀፍ የባህር ሕግ ስምምነቶች መሠረት ወደ ባህር የመድረስ እና የመጠቀም መብት ቢኖራቸውም፣ በተግባር ግን ከባህር ዳርቻ ሀገራት ጋር በሚደረጉ የሁለትዮሽ ስምምነቶች ላይ ጥገኛ ናቸው።

እኛ ደግሞ የባህር በር የነበረን ሀገር ነን፡፡ ባለቤት ለመሆን ጉዳዩን የአደባባይ አጀንዳ ካደረግን በኋላ ዓለም እየደገፈን ይገኛል፡፡ የዚህን የዲፕሎማሲ ድል ድርብ የምናደርገው ደግሞ የራሳችን የባህር በር ሲኖረን ነው፡፡ ያኔ የደህንነት እና የኢኮኖሚ ሉዓላዊነታችንን ሙሉ በሙሉ እንጎናጸፋለን፡፡

Exit mobile version