Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በዓለም ዋንጫ ከታዩ ያልተጠበቁ ድሎች አንዱ – ካሜሩን ከአርጀንቲና

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ከ36 ዓመታት በፊት የካሜሩን ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች በዛሬዋ ዕለት በዓለም ዋንጫ ውድድር የማይረሳ ታሪክ ጽፈዋል፡፡

በፈረንጆቹ 1990 ጣሊያን ባዘጋጀችው የዓለም ዋንጫ የመክፈቻ ጨዋታ አርጀንቲና እና ካሜሩን በሳን ሲሮ ስታዲየም ተገናኝተዋል፡፡

በወቅቱ ድንቅ ብቃት ላይ በነበረውና በዲያጎ አርማንዶ ማራዶና የሚመራው የአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድን ለጨዋታው ቅድመ ግምት አግኝቷል፡፡

የእግር ኳስ ተንታኞችና ግምቶች ሁሉ ወደ አርጀንቲና ያመዘኑ ሲሆን ÷ ማንም ከአፍሪካ ለመጣው የካሜሩን ብሔራዊ ቡድን ቦታ አልነበረውም።

የካሜሩን ብሔራዊ ቡድን በወቅቱ በዓለም ዋንጫ መድረክ አንድም ጨዋታ አሸንፎ አያውቅም፤ በ1982 ተሳትፎውም ሦስት የአቻ ውጤት አስመዝግቦ ነው የተመለሰው፡፡

ሆኖም የካሜሩን ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች (የማይበገሩት አንበሶች) ወደ ጣሊያን የመጡት ለሽርሽር አልነበረም፤ ታሪክ ለመጻፍ እንጂ።

የመጀመሪያው አጋማሽ የሁለቱ ቡድኖች ፍልሚያ በጠንካራ ፉክክር 0 ለ 0 አቻ ተናቀቀ፡፡

በ61ኛው ደቂቃ ላይ ካሜሩናዊው ተጫዋች አንድሬ ካና ቢይክ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናበተ።

በ10 ተጫዋቾች ማራዶናን እና አጋሮቹን መቋቋም የማይታሰብ ይመስል ነበር።

ሆኖም ፍራንሷ ኦማም ቢይክ ከቅጣት ምት የተሻገረለትን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ በማስቆጠር ካሜሩንን መሪ ማድረግ ቻለ፡፡

ከግቧ መቆጠር በኋላ ሌላኛው ካሜሩናዊ ተጫዋች ቤንጃሚን ማሲንግ በቀይ ካርድ አይቶ ከሜዳ ተሰናበተ፡፡

ካሜሩን ጨዋታውን 1 ለ 0 ማሸነፍ የቻለች ሲሆን÷ ድሉም የአፍሪካ እግር ኳስ መልክ የቀየረ ነበር፡፡

ጨዋታው በዓለም ዋንጫ ታሪክ ውስጥ ከታዩ ታላላቅ ያልተጠበቁ ድሎች አንዱ ሆኖ በታሪክ ይወሳል፡፡

በወርቅነህ ጋሻሁን

Exit mobile version