አዲስ አበባ፣ ሰኔ 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሸገር ከተማ ከፍተኛ ፍ/ቤት ወንጀል ችሎት ገቢ በመሰወር እና በሀሰተኛ የንግድ ፍቃድ ማረጋገጫ ዓመታዊ ግብር በመሰወር ወንጀል የተከሰሱ ተከሳሾች በጽኑ እስራትና በገንዘብ እንዲቀጡ ወስኗል።
ተከሳሾቹ 1ኛ የሱሉልታ ክ/ከተማ የገቢዎች ጽ/ቤት ባለሙያ የነበረው ተክሌ ተስፋ ሞሲሳ፣2ኛ የሸቀጣ ሸቀጥ ንግድ ሥራ ላይ የተሰማራው ተስፋዬ በቃና ፈይሳ፣ 3ኛ የስጋ ቤት ንግድ ላይ የተሰማራው ዘሪሁን ብርሻው ፈረጃ፣ 4ኛ ጌት ኢንተርናሽናል የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋም እና 5ኛ ተከሳሽ የዚሁ ተቋም ሥራ አስኪያጅ ተሰማ አበበ ኤጀርሳ ናቸው።
የሸገር ከተማ ዐቃቤ ሕግ ጽ/ቤት የኢኮኖሚ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በተከሳሾቹ ላይ የተሳትፎ ደረጃቸውን ጠቅሶ ሀሰተኛ ሰነድ መገልገል እንዲሁም የታክስና የግብር አስተዳደር ሕግን መተላለፍ የሚል ዝርዝር ክስ አቅርቦባቸው ነበር።
በዚህም 1ኛ ተከሳሽ የሱሉልታ ክ/ከተማ የገቢዎች ጽ/ቤት ባለሙያ ሆኖ ሲሰራ ከቀሪ ነጋዴ ተከሳሾች ጋር በመመሳጠር የሁለት ዓመት ዓመታዊ ግብር ባልገበሩበት ሁኔታ ላይ ግብር እንደገበሩ አስመስሎ ሀሰተኛ ማረጋገጫና ሀሰተኛ ደረሰኝ አዘጋጅቶ መስጠቱ በክሱ ተጠቅሷል።
በተጨማሪም በ1ኛ ተከሳሽ መኖሪያ ቤት በጸጥታ አካላት በተደረገ ብርበራ ሀሰተኛ የገቢዎች ጽ/ቤት ማሕተምና ሀሰተኛ ሰነዶች መገኘታቸው በክሱ ተመላክቷል፡፡
በዚህ መሰረት ቀሪ ተከሳሾች ደግሞ ያገኙትን ሀሰተኛ የግብር ማረጋገጫና የቫት ደረሰኝ በመጠቀም በተለያዩ መጠኖች ከሸማቶች የሰበሰቡትን በመሰወር ማለትም 2ኛ ተከሳሽ 8 ሺህ 536 ብር፣ 3ኛ ተከሳሽ 101 ሺህ 798 ብር የቫት ገቢ በመሰወር፣ 4ኛ ተከሳሽ 556 ሺህ 391 ሺህ ብር ግብር በመሰወር እንዲሁም 5ኛ ተከሳሽ በሀሰተኛ ማረጋገጫ ንግድ ፍቃድ ማደስ በሚል የተሳትፎ ደረጃቸውን ጠቅሶ ዐቃቤ ሕግ በክሱ ዝርዝር ላይ አስፍሯል።
ተከሳሾቹ በዚህ መልኩ የቀረበባቸውን ክስ ክደው መከራከራቸውን ተከትሎ ዐቃቤ ሕግ የሰነድና የሰው ማስረጃ አቅርቧል።
ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ ሕግ ያቀረበውን ማስረጃ መርምሮ ተከሳሾቹ እንዲከላከሉ ብይን የሰጠ ቢሆንም ተከሳሾች የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን መከላከል ባለመቻላቸው የጥፋተኝነት ፍርድ ተላልፎባቸዋል።
ከዚህም በኋላ የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየት በመመርመርና በመያዝ ፍርድ ቤቱ በቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁጥር 3/2017 መሰረት 1ኛ ተከሳሽ በ8 ዓመት ከ4 ወራት ጽኑ እስራትና በ4 ሺህ ብር እንዲቀጣ ወስኗል፡፡
በተጨማሪም 2ኛ ተከሳሽ በ2 ዓመት ከ6 ወራት ጽኑ እስራትና በ20 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲሁም 3ኛ ተከሳሽ በ8 ዓመት ከ4 ወራት ጽኑ እስራትና በ20 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ተወስኗል።
ፍርድ ቤቱ 4ኛ ተከሳሽ ላይ የ500 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት የወሰነ ሲሆን÷ የተቋሙ ሥራ አስኪያጅ 5ኛ ተከሳሽ ደግሞ በ2 ዓመት ከ9 ወራት እስራት እና በ10 ሺህ ብር እንዲቀጣ ወስኗል።
በታሪክ አዱኛ

