አዲስ አበባ፣ ሰኔ 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ከተካሄደባቸው የምርጫ ክልሎች ውስጥ የ24ቱን ውጤቶች አጽድቄያለሁ አለ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላተወርቅ ኃይሉ ዛሬ ማምሻውን በሰጡት መግለጫ፥ ከሁለት ምርጫ ክልሎች ውጭ በሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች ውጤት መለጠፉን ጠቁመዋል።
ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም በተካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የድምፅ መስጠት ሒደት ከተጠናቀቀ በኋላ የምርጫ ጣቢያዎችና የምርጫ ክልሎች ውጤትን የማዳመር ስራ ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
በዚህም መሰረት በ24 የምርጫ ክልሎች የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የክልል ምክር ቤቶችን ውጤት ማፅደቁን ቦርዱ አስታውቋል።
እነዚህ የምርጫ ክልሎችም በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ እና ጋምቤላ ክልሎች የሚገኙ መሆናቸው ነው የተገለጸው።
በሔብሮን ዋልታው

