አዲስ አበባ፣ ሰኔ 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የታክስ አስተዳደር ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ የታክስ አሰራርን በማዘመን ፍትሐዊነትና የሕግ ተገዢነትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል አለ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ።
ቋሚ ኮሚቴው የታክስ አስተዳደር ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር የአስረጂ መድረክ አካሂዷል።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ፍቃዱ ሆረታ በዚህ ወቅት÷ የታክስ አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ ከኢትዮጵያ ፈጣን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ጋር የተጣጣመ ዘመናዊ የታክስ አሰራር ለመፍጠር ያስችላል ብለዋል።
በታክስ ከፋዩ ማህበረሰቡ የሚነሱ መሰረታዊ የፍትሐዊና የመልካም አስተዳደር ቅሬታዎችንም መፍትሔ ለመስጠት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ገልጸዋል።
የመንግሥትን ገቢ የመሰብሰብ አቅም በማጎልበት ተጠያቂነትን ከግልጽነት ያጣመረ ዘመናዊ የአሰራር ሥርዓት መዘርጋት እንደሚያስችልም ተናግረዋል።
የምክር ቤቱ አባላትና የሕግ ማዕከል ባለሙያዎችም በማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ የታክስ ስሌት፣ የይርጋ ጊዜ ገደብ፣ የታክስ ከፋይ መስተንግዶና ተያያዥ ጉዳዮችን በማስመልከት ጥያቄ አንስተዋል።
በገንዘብ ሚኒስቴር ከፍተኛ የሕግ አማካሪ ዋሲሁን አባተ በረቂቅ አዋጁ የይርጋ ጊዜው 10 ዓመት ሆኖ መቀመጡ በታክስ ከፋዩ ላይ የሚኖረውን ጫና መቀነስ እንደሚያስችል ተናግረዋል።
በገንዘብ ሚኒስቴር የሕግ ጉዳዮች መምሪያ ኃላፈ ተወዳጅ መሐመድ የታክስ ደረሰኝ አለመስጠት ተመሳሳይ የገንዘብ ቅጣት መጣሉ ሆን ተብሎ የሚፈጸምን የታክስ ማጭበርበር በማስቀረትና ደረሰኝ መቁረጥን ባህል ያደርጋል ብለዋል።
በገቢዎች ሚኒስቴር የታክስ አማካሪ ያሬድ ፍቃደ በበኩላቸው እንዳሉት÷ የገለልተኛ አስማሚ ስርዓት ገለልተኛ ሆኖ የሚቋቋም በመሆኑ ግብር ከፋዩ የሚገጥመውን ችግር መፍቻ ተጨማሪ አማራጭ ነው።
የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ደሳለኝ ወዳጀ የማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ ኢኮኖሚው በሚያመነጨው ልክ ገቢን ለመሰብሰብና የታክስ አስተዳደርን ለማዘመን እንደሚያስችል መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በአስረጂ መድረኩ ግልፅ ያልሆኑ ጉዳዮች ይበልጥ ማጥራት የሚያስችል ማብራሪያ መሰጠቱን ጠቁመው÷ የተደረጉት ማሻሻያዎች ፍትሐዊነትንና የሕግ ተገዢነትን የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።

