አዲስ አበባ፣ ሰኔ 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አሜሪካ በኢራን ላይ ጥቃት መፈጸሟን ተከትሎ ቴህራን የሆርሙዝ ሰርጥን በድጋሚ ሙሉ ለሙሉ መዝጋቷን አስታውቃለች፡፡
በዚህ መሰረትም የኢራን ጦር የሆርሙዝ የባሕር ዳርቻ ሙሉ በሙሉ እንዲዘጋ የወሰነ ሲሆን ÷ ነዳጅ ጫኚ እና የንግድ መርከቦች እንቅስቃሴ እንዲገታም ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
አሜሪካ በኢራን ላይ ጥቃት መፈጸሟን ተከትሎ የኢራን ጦር በአካባቢው በሚገኙ የአሜሪካ ኃይሎች ላይ የአጸፋ ጥቃት ፈጽሟል፡፡
ከአሜሪካ ጥቃት በኋላ የኢራን ጦር በኩዌት፣ ባህሬን እና ዮርዳኖስ የሚገኙ የጦር ሰፈሮችን ኢላማ ማድረጉ ነው የተገለጸው፡፡
የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ ቀደም ሲል በኢራን ውስጥ ባሉ በርካታ ኢላማዎች ላይ ጥቃት የፈጸመ ሲሆን ÷ ጥቃቱ እራስን ለመከላከል ያለመ ነው ሲል ገልጿል፡፡
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወታደሮቹ ኢራንን ለማጥቃት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ጠቁመው÷ አሁን ዋጋ መክፈል አለባቸው ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
የኢራን መገናኛ ብዙኃን የወደብ ከተማ ባንደር አባስ፣ ቄሽም ደሴት እና ከቴህራን በስተ ምዕራብ በሚገኙት ሲሪክ፣ ሚናብ እና ካራጅ ደቡባዊ ከተሞች ላይ ጥቃት መሰንዘሩን ዘግበዋል፡፡
በሌላ በኩል የእስራኤል ጦር በሊባኖስ ላይ የሚፈጽመው ጥቃት የቀጠለ ሲሆን÷በሀገሪቱ ደቡብ እና በበካቫሊ አካባቢ በደረሰው ጥቃት በርካታ ጉዳት ማድረሱ ተመላክቷል፡፡
በወንድማገኝ ጸጋዬ

