Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ልዩነትን በውይይት መፍታት ለሰላም ብቸኛው ተስፋ ነው – አንቶኒዮ ጉቴሬዝ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሃሳብ ልዩነት የሚፈጠሩ ግጭቶችን በውይይት መፍታት ተመራጩ እና ሰላምን ለማረጋገጥ ብቸኛው ተስፋ ነው አሉ የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ።

ዓለም አቀፍ የስልጣኔዎች የውይይት ቀን በትናንትናው ዕለት በተለያዩ ሁነቶች ተከብሯል፡፡

አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በዚህ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት ፥ዓለም አቀፋዊ ችግሮችን ለመፍታት እና ሰላምን ለማጽናት ውይይት ከፍተኛ አቅም እንዳለው አስገንዝበዋል፡፡

ከመካከለኛው ምስራቅ እስከ ዩክሬን እንዲሁም በሱዳን እና ሌሎች አካባቢዎች ግጭትን ለመፍታትና የሰዎችን ሕይወት ለመታደግ የውይይት ሒደት አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

ከውይይት ውጭ አማራጭ የለም፤ ይህንን ለማድረግም የምናባክነው ጊዜ ሊኖር አይገባም ነው ያሉት ዋና ጸሐፊው፡፡

ስንደማመጥ፣ ስንነጋገርና ስንገናኝ እርስ በርስ መጋጨትን በመተባበር፤ ውጥረትን ደግሞ በመተማመን መተካት እንችላለን ሲሉ ተናግረዋል።

ዓለም አቀፍ የስልጣኔዎች የውይይት ቀን በየዓመቱ በፈረንጆቹ ሰኔ 10 ቀን በተለያዩ ሁነቶች ይከበራል።

በፈረንጆቹ 2024 በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ የታወጀው ይህ ቀን የብዝሃ ስልጣኔ አስፈላጊነትን በማክበር፤ በውይይት የዓለም ሰላምን፣ የጋራ መግባባትን እና ዓለም አቀፋዊ ትብብርን ለማጠናከር ያለመ ነው።

በብርሃኑ አበራ

Exit mobile version