Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በሳዑዲ ለእስር ተዳርገው የነበሩ 1655 ኢትዮጵያውያን የምህረት አዋጅ ተሰጣቸው

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሳዑዲ አረቢያ ለእስር ተዳርገው የነበሩ 1655 ዜጎቻችን የፍርድ ሂደታቸው ተቋርጦ የምህረት አዋጅ እንዲሰጣቸው ተደርጓል አለ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር።

ለኢትዮጵያውያኑ ምህረት የተደረገው ሚኒስቴሩ በሪያድ የኢትዮጵያ ኤምባሲና በጂዳ የሚገኘውን ቆንስላ ጽ/ቤት በማስተባበር ባደረገው የዲፕሎማሲ ጥረት መሆኑን ገልጿል፡፡

ይህ ውጤት መንግሥት በውጭ ግንኙነቱ ለዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ በሰጠው ትኩረት የተገኘ መሆኑንም ሚኒስቴሩ አመልክቷል፡፡

ከዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ አኳያ በሳዑዲ አረቢያ ቀሪ የዲፕሎማሲ ጥረት የሚሹ ጉዳዮችን በተመለከተም ክትትል እየተደረገ መሆኑም ነው የተገለጸው፡፡

መንግሥት ሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ከውጭ ሀገር ጉዞ ጋር በተገናኘ በማኅበራዊ ሚዲያና ሌሎች መንገዶች ከሚያሰራጯቸው ሀሰተኛ ማታለያዎች ሕብረተሰቡ ራሱን እንዲጠብቅ አሳስቧል፡፡

ሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን የሕግ ተጠያቂ ለማድረግ የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል፡፡

Exit mobile version