አዲስ አበባ፣ ሰኔ 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ) በሶማሌ ክልል በለውጡ ዓመታት የተመዘገቡ የልማት ስኬቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የበኩሌን አስተዋጽኦ ለማበርከት ዝግጁ ነኝ አለ፡፡
የኦብነግ ምክትል ሊቀመንበር አሕመድ ያሲን÷ ከለውጡ በፊት በሶማሌ ክልል በነበረው አግላይና ፍትሃዊነት በጎደለው የፖለቲካ ሥርዓት ሳቢያ ኦብነግ የጫካ ትግል ውስጥ እንደነበር አስታውሰዋል።
ይሁን እንጂ በሀገሪቱ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ በተፈጠረው ምቹ የፖለቲካ ምህዳር የትጥቅ ትግሉን በመተው ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል በማድረግ ላይ ይገኛል ብለዋል።
በዚህ የትግል ሒደት የሃሳብና የፖሊሲ ልዩነቶች እንደተጠበቁ መሆናቸውን አንስተው÷ በሀገር ሉዓላዊነት፣ በብሄራዊ ጥቅምና በዜጎች ሰላምና ደህንነት ጉዳይ ላይ የተለየ አቋምና አመለካከት የለንም ሲሉ አስረድተዋል።
በሶማሌ ክልል በለውጡ ዓመታት ለመጣው ዘላቂ ሰላም፣ የሚታዩና የሚጨበጡ የልማት ስራዎች ፓርቲያቸው አድናቆት እንዳለው ነው የገለጹት፡፡
ይህ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርቲያቸው የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ለኢዜአ ገልጸዋል።
በፓርቲው ስም ከታጠቁ ኃይሎች ጋር ጥምረት በመፍጠር የባዕድ ተልእኮ በመቀበል ለጥፋት የሚንቀሳቀሱ ባንዳዎች መኖራቸውን አንስተዋል።
እንዲህ አይነት የጥፋት ተልዕኮ አንግበው የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች በኦብነግ ውስጥ ምንም አይነት ስፍራ የላቸውም፤ በጋራ እንታገላቸዋለን ነው ያሉት፡፡
ኦብነግ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በመሳተፍ በክልሉ ያለውን ጠንካራ የፖለቲካ ተሳትፎ ማሳየቱን ገልጸው÷ በሰላማዊ ትግል ለዴሞክራሲ ሥርአት ግንባታ ሒደት የበኩሉን መወጣቱን ይቀጥላል ብለዋል።
በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ሃይሎች በለውጡ የተፈጠረውን ምቹ የፖለቲካ ምህዳር በአግባቡ በመጠቀም ለሀገር ጥቅምና ለሁለንተናዊ እድገት አጋዥና ደጋፊ በመሆን መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

