Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የተፈጥሮ ሃብትን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ጋር ማጣመርና ማልማት…

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የተፈጥሮ ሃብትን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ጋር ማጣመርና ማልማት ይገባል አለ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል 3ኛው ዙር ክልል አቀፍ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና የፈጠራ ስራዎች ውድድር አውደ ርዕይ እና የፓናል ውይይት እየተካሄደ ነው።

በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ (ዶ/ር) ባለፉት ዓመታት በዘርፉ ያሉ ፀጋዎችን ወደ ሃብት መቀየር የሚያስችሉ ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።

ዘርፉ ዜጎችን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ከማድረግ ባሻገር ሃብት ለማመንጨት ትልቅ አቅም እንዳለው ገልጸው÷ ወጣቶች ስራ ፈላጊዎች ሳይሆኑ ስራ ፈጣሪ እንዲሆኑ እየተሰራ ያለውን ተግባር አጠናክሮ መቀጠል ይገባል ብለዋል።

መንግሥት ለስራ ፈጣሪዎች እውቅና በመስጠት የፋይናንስና ሌሎች ድጋፎችን እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር በርካታ ስራዎች መከናወናቸውንም ጠቁመዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፈቃዱ በበኩላቸው÷ በክልሉ ባለፉት ዓመታት በርካታ የፈጠራ ስራ ውጤት መገኘቱን ገልጸዋል።

በአውደ ርዕዩ ላይ 146 የፈጠራ ስራዎችና ቴክኖሎጂዎች ቀርበው እንደሚወዳደሩም ጠቁመዋል።

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አየለች እሼቴ ሳይንስ ለሀገር እድገትና ብልፅግና ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑን አንስተው÷ የፈጠራ ሐሳቦች ወደ ኢንዱስትሪ የሚቀየሩበትን ምህዳር ለመፍጠር እየተደረገ ያለውን ትጋት በበለጠ አጎልብቶ መቀጠል እንደሚገባ አመላክተዋል።

በብርሃኑ በጋሻው

Exit mobile version