Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ለአርሶ አደሩ የዲጂታል መረጃ ሥርዓት ተደራሽነትን ለማጠናከር እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ለአርሶ አደሩ የዲጂታል መረጃ ሥርዓት ተደራሽነትን ይበልጥ በማጠናከር ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው አለ የግብርና ሚኒስቴር፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የዲጂታል ግብርና ኤክስቴንሽን እና የምክር አገልግሎት ፎረም ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ተካሂዷል፡፡
በግብርና ሚኒስቴር የእርሻና ሆርቲካልቸር ሚኒስትር ዴዔታ አማካሪ አሊ መሃመድ (ፕ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት÷የግብርና ዘርፉን ውጤታማነት ይበልጥ ለማሻሻል በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡
በዘመኑ ቴክኖሎጂ በመታገዝ ለአርሶ አደሩ ወቅቱን የጠበቀ የግብርና መረጃ ተደራሽ ለማድረግ በቁርጠኝነት መሰራቱን ተናግረዋል፡፡
ለደረጃው የሚመጥን የዲጂታል ግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት ትብብርን፣ ቅንጅትንና ፈጠራን እንደሚጠይቅ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ግብን በአነስተኛ አርሶ አደሮች ማሳ ላይ ለማሳካት ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ የግብርና ኤክስቴንሽን ሥርዓት በሀገሪቱ የግብርና እና ገጠር ልማት ስትራቴጂ ምሰሶዎች መካከል በግንባር ቀደምትነት እንደሚጠቀስ አመልክተዋል፡፡
ይሁን እንጂ አሁን ላይ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በገበያ አለመረጋጋት እና ምርታማነትን በፍጥነት የመጨመር አስፈላጊነት ምክንያቶች እየተፈተነ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
ችግሩን ለመፍታት የዲጂታል ግብርና ፍኖተ ካርታ ሥራ ላይ መዋሉን ጠቁመው÷ ውጤታማ የኤክስቴንሽንና የምክር አገልግሎትን ለመስጠት በፍጥነት እያደገ ካለው የዲጂታል ሥነ ምህዳር ጋር መጣጣም ይገባል ብለዋል፡፡
በሚኒስቴሩ የእርሻና ሆርቲካልቸር ኤክስቴንሽን መሪ ሥራ አስፈፃሚ የኔነሽ ኤጉ በበኩላቸው ÷ የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎትን ለማሳደግ ዲጂታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በተለይም ለአርሶ አደሩ ከመሬት ዝግጅት እስከ ድህረ ምርት እንዲሁም በገበያ አቀራረብ ላይ ሙያዊ ምክር እየተሰጠ ይገኛል ነው ያሉት፡፡
ይህም አርሶ አደሩ ወቅቱን የጠበቀ መረጃ እንዲኖረው በማድረግ ምርታማነቱ እንዲጨምር እያደረገ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
የግብርና መረጃ አገልግሎት በ8028 ነጻ የሥልክ መስመር ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እየሆነ ነው ያሉት ደግሞ በኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዲጂታል ግብርና ፍኖተ ካርታ ፕሮጀክት አስተባባሪ አንዱአለም ዋለልኝ ናቸው፡፡
በ6 ቋንቋዎች አገልግሎት እየሰጠ በሚገኘው የነጻ ጥሪ ማዕከል እስካሁን ከ68 ሚሊየን በላይ ጥሪዎች መስተናገዳቸውንም አመልክተዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ
Exit mobile version