Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የክልሎች ዝግጅት ለአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር…

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኦሮሚያ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ለ2018 ዓ.ም የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረግን ነው አሉ፡፡

የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ም/ ኃላፊ አቶ በሪሶ ፈይሳ እንዳሉት ÷ የዘንደሮውን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብርን በስኬት ለማጠናቀቅ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡

ለመርሐ ግብሩ በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ከ5 ቢሊየን በላይ ችግኞች ለማዘጋጀት እየተሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡

ለአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብሩ ከ1 ሚሊየን ሔክታር በላይ መሬት መዘጋጀቱን አቶ በሪሶ ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ግብርና ቢሮ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ ደሳለኝ በበኩላቸው ÷ በ2018 ዓ.ም የአረንጓዴ ዐሻራ ከ80 ሚሊየን በላይ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

ችግኞቹ በክልሉ በሚገኙ 79 ጣቢያዎች እየተዘጋጁ ሲሆን ÷ ለተከላ ዝግጁ የሆኑ ቸግኞችን የመለየት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ለተከላ የሚዘጋጁት ችግኞች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው መሆናቸውን የጠቆሙት አመራሮቹ ÷ የጉድጓድ ቁፋሮ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በተለይም የቡና፣ የፍራፍሬ፣ የጥምር ደን እና ሌሎች የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ችግኞች እየተዘጋጁ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በተጨማሪም ለችግኝ መትከያ ቦታዎች የካርታ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን የማዘጋጀት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የታቀደውን ሥራ በስኬት ለማጠናቀቅ የክልሎቹ ሕዝብ በንቃት እንዲሳተፍ ጥሪ ቀርቧል፡፡

Exit mobile version