Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

መዲናዋን የጤና ቱሪዝም ማዕከል ያደረጓት ዘመናዊ የጤና መሠረተ ልማቶች…

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት ጥቂት ዓመታት በአዲስ አበባ የተገነቡ እና የታደሱ የጤና ተቋማት ከተማዋ በጤናው ዘርፍ ያላትን የመሠረተ ልማት አቅም ከፍ ከማድረግ ባለፈ ተመራጭ የጤና ቱሪዝም ማዕከል እያደረጓት ነው።

እነዚህ ዘመን ተሻጋሪ እና ትውልድ አኩሪ ስኬታማ ሥራዎች የዘርፉን የአገልግሎት ጥራት እና ተደራሽነት በተጨባጭ ያሳደጉ ናቸው።

የከተማ አስተዳደሩ ለዜጎች ጤና ቅድሚያ በመስጠት መዲናዋን ንጹሕ እና ለመኖር ምቹ ለማድረግ ሰፋፊ ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል።

በዚህም ለእግር ጉዞ፣ ለብስክሌት እና ለተለያዩ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች የተመቹ ሥፍራዎችን በማልማት እንዲሁም ለጤና ጠንቅ የነበሩ የተበከሉ ወንዞችን በማጽዳት እና በማስዋብ በሽታን አስቀድሞ ለመከላከል የሚያስችሉ ስኬታማ ተግባራት ተከናውነዋል።

ከበሽታ መከላከል ሥራዎች በተጨማሪ የዜጎችን ጤና ለመታደግ እና ለማከም የሚያስችሉ ዘመናዊ የሕክምና ማዕከላት ተገንብተዋል።

በምሥራቅ አፍሪካ ቀዳሚ የሆነ የሕክምና ግብዓት የተሟላለት የላፍቶ ዘመናዊ ሆስፒታልን ጨምሮ አዳዲስ ጤና ጣቢያዎች እና ሆስፒታሎች ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል።

በተጓዳኝም እንደ ዘውዲቱ ሆስፒታል ያሉ ነባር የጤና ተቋማት ደረጃቸውን በጠበቀ መልኩ ዳግም የታነጹ ሲሆን÷ በሰው ኃይል እና በዘመናዊ የሕክምና ቁሳቁስ በማደራጀት የዜጎችን ጤና የመጠበቅ ሥራው ተጠናክሮ ቀጥሏል።

እነዚህ ደረጃቸውን የጠበቁ የሕክምና ተቋማት ዜጎች የተሻለ ሕክምና ፍለጋ ወደ ውጭ ሀገራት የሚያደርጉትን ጉዞ በማስቀረት ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ።

በአንጻሩም በቀጣናው ለሚገኙ የጎረቤት ሀገራት ዜጎች ጭምር የተሻለ የሕክምና አገልግሎት የሚሰጥባት የጤና ቱሪዝም ማዕከል መሆን ችመቻሏን የአዲስ አበባ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል።

አዲስ አበባ በጤናው ዘርፍ እያከናወነች የምትገኘው ስኬታማ ሥራ የከተማዋን ሁለንተናዊ ዕድገትና ልዕልና የሚያሳይ ነው፡፡

Exit mobile version