አዲስ አበባ፣ ሰኔ 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) “ሰብአዊ ተግባር ሕይወት ይታደጋል፤ ብርሃን ይመልሳል” በሚል መሪ ሐሳብ የዓለም የደም እና የዓይን ብሌን ለጋሾች ቀን እየተከበረ ነው።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጄ ዱጉማ በዚሁ ወቅት እንዳሉት÷ ሚኒስቴሩ ከበጎ ፈቃደኝነት ጋር በተያያዘ ሰፋፊ ስራዎች ሰርቷል።
በዚህም በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ60 በላይ ደም ባንኮች መቋቋማቸውን አንስተው÷ የደም ልገሳ አሁን ላይ ባህል እየሆነ መጥቷል ብለዋል።
ደም የመለገስ ተግባር አሁንም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ደም እና ሕብረ ሕዋስ ባንክ አገልግሎት ዋና ስራ አስኪያጅ ዶ/ር አሸናፊ ታዘበው በበኩላቸው÷ በበጀት ዓመቱ ከ441 ሺህ ዩኒት በላይ ደም መሰብሰብ መቻሉን ጠቁመዋል።
ይህም ከባለፈው በጀት ዓመት አንጻር የ19 በመቶ እድገት እንዳለው ገልጸው÷ በበጀት ዓመቱ 338 የዓይን ብሌን ለማሰባሰብ ታቅዶ ከ411 በላይ ማሰባሰብ መቻሉንም ተናግረዋል።
የሰኔ ወር እስከሚጠናቀቅ ድረስ የደም እና የዓይን ብሌን ለጋሾች ቀን በተለያዩ መርሐ ግብሮች እንደሚታሰብ ተመላክቷል።
በቅድስት ብርሃኑ

