ለሰከነ ውይይትና መግባባት ቅድሚያ የሚሰጡ ባህላዊ እሴቶቻችን ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬት ተጨማሪ አቅም ናቸው፡፡
ህብረተሰባችን በየራሱ ባህል አለመግባባቶችን በሰከነ ውይይት መፍትሄ የሚያበጅበት የየራሱ የዳበረ እሴት አለው፡፡
ባህላዊ እሴቶቻችን ለሃገረ መንግሥት ግንባታና ለሰላም ያላችው አበርክቶም ከፍተኛ ነው፡፡
እሴቶቹ ምቹ የምክክር መድረክን በመፍጠር ለአለመግባባቶች በሰከነ ውይይት መፍትሄ እንዲያገኙ ያደርጋሉ፡፡
ለሀገራዊ ምክክር ስኬትም አቅም ናቸው፤ በህብረተሰቡ ውስጥ ሰላማዊ ግንኙነትንም ያጠናክራሉ።
በዚህም የጌዴኦ የ”ጋፌ” ሥርዓት ተጠቃሽ ነው።
የጌዴኦ ባህላዊ የዳኝነት ስርዓቱ “ጋፌ” ያለምንም ልዩነት እውነትን መሠረት ያደረገ ፍትህን በማውረድ የህዝቡን ሠላም ማስጠበቅ የቻለ እሴት ነው፡፡
የጌዴኦ ብሔረሰብ ባህላዊ አስተዳደራዊ ሥርዓት “ባሌ” በመባል ይታወቃል፡፡
ከዚህ ሥርዓት የሚመነጨውና እውነትንና ሰላምን ለማስፈን የሚተገበረው ባህላዊ የዳኝነት ሥርዓት ደግሞ “ጋፌ” ይባላል።
የዳኝነት ስርዓቱ የሚፈፀምበት ስፍራ “ሶንጎ” የሚባል ሲሆን፣ ለዚሁ ተግባር የሚሰየሙ ዳኞች ባጤቲ ሃይቻዎች እና ሁላቲ ሃይቻዎች ናቸው፡፡
ባህላዊ የዳኝነት ስርዓቱ በማህበረሰቡ ውስጥ የሚከሰት አለመግባባቶችን በሰከነ መንገድ ለመፍታት ፍቱን ነው፡፡
ቅሬታና አለመግባባት በመነጋገር ይፈታል፤ ፍትህን ፈልጎ ሶንጎ የሄደና ጋፌ ፊት የቀረበው ሁሉ ያለልዩነት ፍትህን ያገኛል፡፡
ተበዳይ ይካሳል፤ ማህበረሰቡም በሰላም አብሮ ይኖራል፡፡
ጋፌ ለውይይትና ለመግባባት ቅድሚያ ይሰጣል፡፡ ልዩነቶች ሁሉ በባህላዊ ሥርዓቱ በሰከነ መንገድ በመነጋገር ይፈታሉ፡፡
ባህላዊ የዳኝነት ስርዓቱ የመደበኛ ፍርድ ቤቶችን ሸክምም ያቀለለና የጊዜ ብክነትንም ያስቀረ ነው፡፡
በሀገራችን ያሉና ለሰከነ ውይይትና መግባባት ቅድሚያ የሚሰጡ ሀገር በቀል እውቀቶች፣ ችግሮችን በሰከነ መንገድ ተነጋግሮ የመፍታት ባህሉ እንዳለን ማሳያ ናቸው፡፡
ሀገር በቀል እውቀቶች የማህበረሰቡን መልካም እሴቶችንና ባህሎችን ለማጎልበት አስተዋጽኦዋቸው ከፍተኛ ነው።
በተለይም ለዘላቂ ሠላም መሠረት የሆኑ የጋራ እሴቶች እንዲጎለብቱ በማስቻል ረገድ ሰላምንና መከባበርን ለማፅናት ያግዛሉ፡፡
ተነጋግረን፣ ተመካክረን ልዩነቶቻችንን እንፍታ! ኑ፤ ሀገር እንሥራ!

