Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በፈረንሳይ የነበሩ ከ100 በላይ የቅሪተ አካላት ናሙናዎች ተመለሱ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በፈረንሳይ የነበሩ ከ100 በላይ የቅሪተ አካላት ናሙናዎች ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል አለ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን፡፡

ባለስልጣኑ በፈረንሳይ የሳይንሳዊ ጥናት ማዕከል ለዓመታት ተጠብቀው የቆዩ የቅሪተ አካላት ናሙናዎችን ተረክቧል።

በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር አሌክሲስ ላሜክ በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ በኢትዮጵያ መሬት የተገኙት ቅሪተ አካላት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ለመላው የሰው ልጅ ልዩ ቅርስ ናቸው ።

አምበሳደሩ በ70ዎቹ እና 80ዎቹ በኦሞ ሸለቆና በአፋር ክልል የተገኙት እነዚህ ናሙናዎች መመለሳቸው ቅርሶች በተገኙበት ሀገር ተጠብቀው እንዲቆዩ ያለውን የሁለቱን ሀገራት የጋራ ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም የኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ ተመራማሪዎች የሰው ልጅን አመጣጥ ለመረዳት ላለፉት አስርት ዓመታት ሲያደርጉት የቆዩትን የጋራ ሳይንሳዊ ጥረት የሚያስታውስ መሆኑንን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አበባው አያሌው በበኩላቸው ÷ የናሙናዎቹ መመለስ ለሀገሪቱ የቅርስ ጥናትና ምርምር ሥራ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል።

የቅርሶች ልውውጥ በፈረንሳይ እና ኢትዮጵያ መካከል በሳይንስ፣ በባህል እና በቅርስ ጥበቃ ዘርፍ ያለውን የረጅም ጊዜ አጋርነት እንደሚያሳይ አውስተዋል፡፡

ፈረንሳይ የኢትዮጵያን ባህል እና ሳይንሳዊ ቅርስ በመጠበቅና በማስተዋወቅ ረገድ ድጋፏን አጠናክራ መቀጠሏንም አመልክተዋል።

በግዛቸው ግርማዬ

Exit mobile version