አዲስ አበባ፣ ሰኔ 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በፈረንጆቹ 1930 መደረግ በጀመረው የዓለም ዋንጫ ውድድር ጀርመናዊው ሚሮስላቭ ክሎስ የመድረኩን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ደረጃን እየመራው ይገኛል፡፡
የጀርመን ብሔራዊ ቡድን የቀድሞ ኮከብ ሚሮስላቭ ክሎስ በዓለም ዋንጫ ውድድር 24 ጨዋታዎችን አድርጎ 16 ግቦችን በማስቆጠር የዓለም ዋንጫ የምን ጊዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪዎች ደረጃን እየመራ ይገኛል፡፡
ሚሮስላቭ ክሎስ በአራት የዓለም ዋንጫ ውድድር ላይ ሀገሩ ጀርመንን ወክሎ የተጫወተ ሲሆን÷ አንድ ጊዜ በመድረኩ ሻምፒዮን ሆኗል፡፡
የብራዚል ብሔራዊ ቡድን የቀድሞ ኮከብ ሮናልዶ ሉዊስ ናዛሪዮ ዴሊማ ደግሞ በ15 ግቦች ይከተላል፡፡ሮናልዶ ሀገሩ ብራዚልን በ4 የዓለም ዋንጫ ውድድሮች የወከለ ሲሆን ሁለት ጊዜ በመድረኩ ሻምፒዮን መሆኑ ይታወሳል፡፡
ተጫዋቹ በዓለም ዋንጫ መድረክ 19 ጨዋታዎችን አድርጎ ነው 15 ግቦችን ማስቆጠር የቻለው፡፡
ሮናልዶ ሉዊስ ናዛሪዮ በፈረንጆቹ 2002 ሀገሩ ብራዚል ዋንጫውን ስታነሳ በ8 ግቦች የውድድሩ ክፍተኛ ግብ አስቆጣሪ በመሆን የወርቅ ጫማ አሸናፊ እንደነበር ይታወሳል፡፡
የጀርመን ብሔራዊ ቡድን የቀድሞ ተጫዋች ገርድ ሙለር 14 ግቦችን በዓለም ዋንጫ በማስቆጠር ከከፍተኛ ግብ አስቆጣሪዎች መካከል አንዱ ነው፡፡
ገርድ ሙለር በዓለም ዋንጫ ውድድር ሁለት ጊዜ የጀርመን ብሔራዊ ቡድንን ያገለገለ ሲሆን÷ አንድ ጊዜ ሻምፒዮን ሆኗል፡፡ተጫዋቹ በሁለት የዓለም ዋንጫ ተሳትፎው 13 ጨዋታዎችን አድርጎ 14 ግቦችን አስቆጥሯል፡፡
ገርድ ሙለር በፈረንጆቹ 1970 በተደረገው የዓለም ዋንጫ ውድድር 10 ግቦችን በማስቆጠር በወቅቱ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ መጨረሱ ይታወሳል፡፡
ፈረንሳዊው የቀድሞ ተጫዋች ጀስት ፎንቴን በታሪኩ በአንድ የዓለም ዋንጫ ተሳትፎ ብቻ 13 ግቦችን ከመረብ አሳርፏል፡፡
ጀስት ፎንቴን በፈረንጆቹ 1958 የዓለም ዋንጫ ላይ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የተሳተፈ ሲሆን÷ 6 ጨዋታዎችን አድርጎ 13 ግቦችን አስቆጥሯል፡፡
በአንድ የዓለም ዋንጫ ውድድር 13 ግቦችን ያስቆጠረው ተጫዋቹ በአንድ የዓለም ዋንጫ መድረክ በርካታ ግቦችን በማስቆጠር ክብረ ወሰኑን ይዟል፡፡
የ2022ቱ የዓለም ዋንጫ ሻምፒዮኑ ሊዮኔል ሜሲ በመድረኩ 13 ግቦችን አስቆጥሯል፡፡
ፈረንሳዊው ኮከብ ኪሊያን ምባፔ ደግሞ 12 ግቦችን በማስቆጠር በመድረኩ ከከፍተኛ ግብ አስቆጣሪዎች መካከል ይገኛል፡፡
ሊዮኔል ሜሲ በ2026ቱ የዓለም ዋንጫ ውድድር 4 ግቦችን ማስቆጠር የሚችል ከሆነ በ17 ግቦች የምን ጊዜም የዓለም ዋንጫ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ደረጃውን ከሚሮስላቭ ክሎስ የሚረከብ ይሆናል፡፡
ኪሊያን ምባፔ በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ 5 ግቦችን ማስቆጠር የሚችል ከሆነ በ17 ግቦች የምን ጊዜም የዓለም ዋንጫ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ደረጃውን ከሚሮስላቭ ክሎስ የሚረከብ ይሆናል፡፡
ሊዮኔል ሜሲ ወይስ ኪሊያን ምባፔ የምን ጊዜም የዓለም ዋንጫ ከፍተኛ ግብ አስቆጣነት ደረጃን ይረከባሉ የሚለው ተጠባቂ ነው፡፡
በወንድማገኝ ጸጋዬ

