Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የፋና ላምሮት ምዕራፍ 22 የድምጻውያን የፍፃሜ ውድድር የፊታችን ቅዳሜ ይካሄዳል

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ላለፉት 3 ወራት በጠንካራ ፉክክር ሲካሄድ የቆየው የፋና ላምሮት ምዕራፍ 22 የድምጻውያን ውድድር የፊታችን ቅዳሜ ሰኔ 13 ቀን 2018 ዓ.ም ፍፃሜውን ያገኛል።

በፋና ላምሮት ፍፃሜ ውድድር ዳንኤል አለልኝ፣ የአብስራ ገዛኸኝ፣ ኤልያስ ገዛኸኝ እና ቃለአብ ገዛኸኝ በሦስት ዙር የመረጧቸውን ሙዚቃዎች ከዛየን ባንድ ጋር ያቀርባሉ።

ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ለእነዚህ ተወዳዳሪዎች የ1 ሚሊየን ብር ሽልማት አዘጋጅቷል።

በውድድሩ 1ኛ ደረጃን ለሚያገኝ የ400 ሺህ ብር፣ 2ኛ ደረጃን ለሚያገኝ ተወዳዳሪ የ300 ሺህ ብር፣ 3ኛ ደረጃን ለሚያገኝ ተወዳዳሪ የ200 ሺህ ብር እና 4ኛ ደረጃን ለሚያገኝ ተወዳዳሪ የ100 ሺህ ብር ሽልማት ተዘጋጅቶላቸዋል።

እነዚህ አራቱ የምዕራፍ 22 የፍፃሜ ተወዳዳሪዎች ለ6ኛው የፋና ላምሮት የአሸናፊዎች አሸናፊ ውድድር በቀጥታ ማለፋቸውን ባለፈው ሳምንት አረጋግጠዋል።

በደማቅ ሥነ ሥርዓት በሚካሄደው የፍፃሜ ውድድር ላይ አንድ ተወዳጅ ድምፃዊ በክብር እንግድነት ይገኛል።

ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽንም አድማጭ ተመልካቾቹን የቅዳሜውን የፍፃሜ ውድድር በፋና ዩቲዩብ እና ፌስቡክ ገጾች እንዲሁም በሁለቱም የፋና ቴሌቪዥን ቻናሎች እንዲከታተሉ ጋብዟል።

ውድድሩን ቅዳሜ ከቀን 6:00 ጀምሮ በቀጥታ ሥርጭት በመከታተል በዕለቱ የሚገለጸውን የተወዳዳሪዎችን ኮድ በ8222 አጭር የጽሑፍ መልዕክት በመላክ እየተዝናናችሁ እንድትደግፉም ግብዣ ቀርቧል፡፡

በለምለም ዮሐንስ

Exit mobile version