Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ሺዎችን ከሳይበር ጥቃት ተከላካይነት እስከ ፈጠራ ባለቤትነት ያሸጋረው የሳይበር ታለንት ቻሌንጅ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት አራት ዓመታት የሳይበር ታለንት ቻሌንጅ ሺዎችን ከሳይበር ጥቃት ተከላካይነት እስከ ፈጠራ ባለቤትነት አሸጋግሯል አለ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር።

ተቋሙ 5ኛው የሳይበር ታለንት ቻሌንጅ ሁለተኛ ዙር ፈተና ከሰኔ 12 እስከ ሰኔ 15 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚሰጥ አስታውቋል።

በአስተዳደሩ የሳይበር ታለንት ዲቪዥን ኃላፊ ስመወርቅ እሸቱ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንዳሉት÷ የሳይበር ታለንት ቻሌንጅ ባለፉት አራት ተከታታይ ዓመታት ሺዎችን ከሳይበር ጥቃት ተከላካይነት እስከ ፈጠራ ባለቤትነት አሸጋግሯል።

ዘንድሮም ሁሉም የሀገሪቱን ክፍል ተደራሽ ለማድረግ በተሰራው ስራ ከ14 ሺህ በላይ ሰልጣኞች ተመዝግበው ከ7 ሺህ በላይ ሰልጣኞች የመጀመሪያውን ዙር ፈተና አጠናቅቀው ወደ ሁለተኛው ዙር ተሸጋግረዋል ብለዋል።

ከምዝገባው ጀምሮ የተዘረጋው አሰራር በቴክኖሎጂ የታገዘ መሆኑ ለአመልካቾች ብቻ ሳይሆን ሰልጣኞችንም ለመመልመል ምቹ እድል ፈጥሯል ነው ያሉት።

የሁለተኛ ዙር ፈተናው በአዳማ፣ ደብረ ብርሃን፣ ባሕርዳር፣ ጅማ፣ ሀሮማያ እና ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲዎች የፊታችን አርብ እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

እንዲሁም ከምስራቅ አፍሪካ ሀገራት፣ ከዩናይትድ አረብ ኤምሬቶች፣ ከአሜሪካ፣ ከእንግሊዝ እንዲሁም ከደቡብ ኮሪያ አመልካቾች መቀበላቸውን ኃላፊው ጠቅሰዋል።

በሐመልማል ዋለ

Exit mobile version