Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የእንግሊዝ መንግሥት የአቪዬሽን ዘርፉን ለማዘመን ያደረገው የቴክኖሎጂ ድጋፍ የጋራ ደኅንነትን ለማረጋገጥ ያግዛል – ሲሳይ ቶላ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የእንግሊዝ መንግሥት የአቪዬሽን ዘርፉን ለማዘመን ያደረገው የቴክኖሎጂ ድጋፍ የጋራ ደኅንነትን ለማረጋገጥ ያግዛል አሉ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል ሲሳይ ቶላ (ዶ/ር)።

የእንግሊዝ መንግሥት የአቪዬሽን ዘርፉን ለማዘመን ያደረገው 25 ሚሊየን ብር የሚያወጣ የቴክኖሎጂ እገዛ የርክክብ መርሐ ግብርና ጉብኝት በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የአቪዬሽን ደኅንነት ዋና መምሪያ ተከናውኗል።

አገልግሎቱ ለፋና ዲጂታል በላከው መረጃ÷ መርሐ ግብሩ በኢትዮጵያ የእንግሊዝ አምባሳደር ዳረን ዌልች የተመራ ልዑካን እንዲሁም የኢትዮጵያ አየር መንገድና የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ነው የተካሄደው።

የአገልግሎቱ ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል ሲሳይ ቶላ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንደገለጹት÷ ድጋፉ በኢትዮጵያና በእንግሊዝ መካከል ያለውን ትብብርና የጋራ ደኅንነትን የማረጋገጥ አጋርነት ማሳያ ነው፡፡

መርሐ ግብሩ በኢትዮጵያና በእንግሊዝ መካከል ያለውን ዘላቂ አጋርነት የሚያሳይ ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑን ገልጸው÷ የአቪዬሽን ዘርፉን ለማዘመን የተደረገው የቴክኖሎጂ ድጋፍ በትብብር ስንሰራ በጋራ ደኅንነትና በዓለም አቀፍ ትስስር አውድ የምናሳካቸውን ድሎች ያሳያል ብለዋል፡፡

የአቪዬሽን ደኅንነት ስጋት ተለዋዋጭና በየጊዜው እያደገ የሚመጣ የዘርፉ ፈተና ነው፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ ያለውን የበላይነት አስጠብቆ ለመዝለቅ የደኅንነት ስጋቶችን አስቀድሞ በማወቅ ማስቀረት ወሳኝ ተልዕኳች ነው ሲሉም ገልጸዋል።

የቴክኖሎጂ ድጋፉም የመፈጸም አቅምን እንደሚያሳድግ አንስተው÷ ኢትዮጵያና እንግሊዝ ትብብራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

በተለይ በቢሾፍቱ የሚገነባው አዲሱ የአየር ማረፊያና ሀገሪቱ በፈረንጆቹ 2027 የምታስተናግደው የኮፕ-32 ጉባኤ በተለያዩ የአጋርነት ማዕቀፎች የሚገለጹ ወሳኝ ሁነቶች መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በዓመት እስከ 120 ሚልየን መንገደኞችን የሚያስተናግድ በአፍሪካ ግዙፍ የሆነውን የአውሮፕላን ማረፊያ እየገነባች ነው ያሉት ሲሳይ ቶላ (ዶ/ር)÷ ይህ ከአቪዬሽን ደኅንነት አንጻር ከፍተኛ ዝግጁነት እንደሚፈልግ ይታወቃል ብለዋል።

በፈረንጆቹ 2027 የምናስተናግደው የኮፕ-32 ጉባኤ ወቅትም የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ዋንኛው እንግዶችን የምንቀበልበት ሥፍራ በመሆኑ ተመሳሳይ የቴክኖሎጂ ትብብሮች እንደሚቀጥሉ ተስፋ እናደርጋለን ነው ያሉት፡፡
በኢትዮጵያ የእንግሊዝ አምባሳደር ዳረን ዌልች በበኩላቸው÷ ሁለቱ ሀገራት እስከ ዛሬ የዘለቀና ጠንካራ የሆነ ወዳጅነት እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡

የአቪዬሽን ዘርፉን ለማዘመን የተደረገው እገዛም ይህንኑ የሚመሰክር እና የሚያጠናክር መሆኑን ገልጸው÷ ኢትዮጵያ በአቪዬሽን ደኅንነት ዘርፍ ያላት ቁመና የሚደነቅ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በየዕለቱ የምታከናውኑት ተግባር የሀገሪቱንም የእኛንም ደኅንነት ስለሚያረጋግጥ አድናቆቴን መግለጽ እወዳለሁ፤ የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ቁልፍ የሆነ የዓለም አቀፍ ተጓዞች መዳረሻና ማዕከል ነው ብለዋል፡፡

ደኅንነትን የማረጋገጥ ጉዳይ የሁላችንም የጋራ ኃላፊነት መሆኑ ይታወቃል ያሉት አምባሳደር ዳረን ዌልች÷ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተከሰቱ ያሉ የበረራ ደኅንነት ስጋቶችን ለመቀነስ ዘመናዊ መሣሪያዎችን መታጠቅ መፍትሔ ስለሚሆን በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ ስራ ላይ የሚውል ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለኢትዮጵያ መበርከቱን ተናግረዋል፡፡

የአቪዬሽን ደኅንነት ዋና መምሪያ ዳይሬክተር አቶ አስራት ቀጄላ ኢትዮጵያ በአቪዬሽን ደኅንነት ዘርፍ ዓለም አቀፍ መመዘኛዎችን በብቃት በማሟላት ተጠቃሽ ሀገር መሆኗን አረጋግጠዋል፡፡

የእንግሊዝ መንግሥት ድጋፍም በተለያየ መንገድ ሲገለጽ መቆየቱን አመልክተው÷ ለተደረገው እገዛም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ከእንግሊዝ መንግሥት ጋር በተለያዩ የተቋማዊ ግንባታ መስኮች ዘርፈ ብዙ ትብብሮችን ስናደርግ ቆይተናል ያሉት ዳይሬክተሩ÷ ትብብሩ ለኢቪዬሽንና ለዓለም አቀፍ አየር ትራንስፖርት ዘርፍ ደኅንነት መረጋገጥ ጉልህ ሚና ወደሚያበረክት ስትራቴጂክ ምዕራፍ ተሸጋግሯል ብለዋል።

የአቪዬሽን ዘርፉን ለማዘመን የተደረገው ድጋፍ ዘመኑን የዋጀ የበረራ ደኅንነትን ለማከናወን ከፍተኛ ሚና እንደሚያበረክት አመልክተው÷ ምስጋቸውን አቅርበዋል፡፡

በኢትዮጵያ የእንግሊዝ ኤምባሲ በኩል የተደረገው ድጋፍ ከሀገሪቱ ሆም ኦፊስ ኢንተርናሽናል ኦፕሬሽን ቢሮ የተገኘ መሆኑን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በላከን መረጃ አስረድቷል፡፡

Exit mobile version