Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

24 ተሽከርካሪዎችን በአንድ ጊዜ ቻርጅ ማድረግ የሚያስችል ማዕከል ተመረቀ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በአንድ ጊዜ 24 ተሽከርካሪዎችን ቻርጅ የሚያደርግ ፈጣን የኃይል መሙያ ማዕከል በአዲስ አበባ ከተማ አስመርቋል።

የአገልግሎቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጌቱ ገረመው (ኢ/ር) ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንዳሉት ÷ ለተጠቃሚዎች አማራጮችን ለማስፋት ግዙፍ የቻርጅ ማድረጊያ ማዕከላት እየተገነቡ ይገኛሉ።

ከ140 ሺህ በላይ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን ጠቁመው ÷ ይሁን እንጂ ከተሽከርካሪዎች ጋር የሚመጣጠን የኃይል መሙያ ማዕከል አለመኖሩን አመልክተዋል።

ይህንን ችግር ለመፍታትም በመጀመሪያው ምዕራፍ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ40 በላይ የኃይል መሙያ ጣቢያዎችን ለመገንባት እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።

እስካሁን የተገነቡት ማዕከላት ሳምንቱን ሙሉ አገልግሎት እንደሚሰጡ የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው ÷ ለተጠቃሚዎች ለአንድ ኪሎ ዋት ሦስት የክፍያ አማራጮች መቅረባቸውን ጠቅሰዋል።

በዚህም ከምሽቱ 4 ሰዓት እስከ ጠዋቱ 12 ሰዓት ድረስ 14 ነጥብ 85 ብር፣ ከጠዋቱ 4 ሰዓት እስከ ቀን 11 ሰዓት ድረስ 16 ነጥብ 57 ብር፣ ከቀኑ 11 ሰዓት እስከ ምሽቱ 4 ሰዓት እንዲሁም ከጠዋቱ 12 ሰዓት እስከ ረፋዱ 4 ሰዓት ድረስ 18 ነጥብ 28 ብር እንደሚያስከፍል ተናግረዋል።

በመሳፍንት እያዩ

Exit mobile version