Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በመዲናዋ የተጀመሩ የተለያዩ የቤት ልማት ፕሮጀክቶች ላይ በትኩረት ይሰራል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ችግርን ለመፈታት የተጀመሩ የተለያዩ የቤት ልማት ፕሮጀክቶች ላይ በትኩረት ይሰራል አሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፡፡
ከንቲባዋ የመዲናዋን የቀጣይ 90 ቀናት እቅድ ባወያዩበት ወቅት እንዳሉት ÷ በአዲስ አበባ ያረጁ የቀበሌ ቤቶችን ደረጃቸውን በጠበቁ የመኖሪያ ቤት ሕንጻዎች የመተካቱ ሒደት ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
ለማሕበረሰቡ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ሲባል በመዲናዋ ያሉ ሰፋፊ ቦታ የያዙ ያረጁ የቀበሌ ቤቶችን በአዲስና በባለብዙ ወለል የመኖሪያ ቤት ሕንጻዎች እንቀይራለን ነው ያሉት፡፡
በቀጣዮቹ ሶስት ወራት በከተማዋ የተጀመሩ የተለያዩ የቤት ልማት ፕሮጀክቶች ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ በጎ ፈቃደኞችን በማስተባበር የሚሰሩ ቤቶችም በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶ የሚሰራባቸው መሆኑን ነው ያመላከቱት፡፡
በተጨማሪም በ2019 ዓ.ም የሚጀመሩ አዳዲስ ቤቶችን ቁጥር መወሰን እና የሚያስፈልገውን ዝግጅት ማድረግ ላይ እንደሚሰራ አስገንዝበዋል፡፡
በዚህም ሰፊ ቦታ የያዙ የቀበሌ ቤቶችን በማፍረስ አዳዲስ ከተማውን የሚመጥኑና ሰፊውን የማሕበረሰብ ክፍል ተጠቃሚ የሚያደርጉ የመኖሪያ ቤት ሕንጻዎች የመገንባት እቅድ መያዙን ጠቁመዋል፡፡
ከዚህ ቀደም የቀበሌ ቤቶች ሲያረጁ ባሉበት ይታደሱ እንደነበር አንስተው÷ ይህ አካሄድ አዋጭ ባለመሆኑ በተለይ ሰፋፊ ቦታ የያዙ የመንግሥት ይዞታ ያላቸው ቦታዎችን ለመኖሪያ ቤት ሕንጻ ግንባታ ማዋል ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ይህም ሰፊውን የማሕበረሰብ ችግር ይፈታል፤ ለከተማ አስተዳደሩም ለልማት ተነሺዎች ትክ ካሳ በመስጠት የሚያወጣውን ወጪ ይቀንሳል ነው ያሉት ፡፡
ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ በሕገ ወጥ መንገድ የተያዙ ቤቶችን የመለየቱ ሥራ በጥንቃቄ እንደሚከናወንም ከንቲባዋ አመልክተዋል፡፡
በአመለወርቅ ደምሰው
Exit mobile version