Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በ86 የምርጫ ክልሎች በቀረቡ ቅሬታዎች ላይ ውሳኔ ተሰጥቷል – ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በፖለቲካ ፓርቲዎች ቅሬታ ከቀረበባቸው 129 የምርጫ ክልሎች ውስጥ በ86ቱ በቀረቡ ቅሬታዎች ውሳኔ ተሰጥቷል አለ፡፡

ቦርዱ በዛሬው ዕለት በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው፥ የቀረቡለትን ቅሬታዎች በፖለቲካ ፓርቲዎች በሚታወቅ ገለልተኛ አካል የማጣራት ሥራ ሲከናወን ቆይቷል፡፡

በዚህም ቅሬታ ከቀረበባቸው 129 የምርጫ ክልሎች ውስጥ በ75 የምርጫ ክልሎች የቀረቡትን ቅሬታዎችና ማስረጃዎች በመመርመር ውድቅ መደረጋቸው ተገልጿል፡፡

በ10 የምርጫ ክልሎች ደግሞ ለቦርዱ ቅሬታ ባቀረቡ አካላት አመልካችነት ቅሬታው ቀሪ መደረጉን የገለጸው ቦርዱ፥ በአንድ የምርጫ ክልል በቀረበው ቅሬታ መሰረት የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች በተገኙበት ድጋሚ የድምጽ ቆጠራ እየተካሄደ መሆኑን አመልክቷል፡፡

በአጠቃላይ ቅሬታ ከቀረበባቸው 129 የምርጫ ክልሎች ውስጥ በ86ቱ ውሳኔ የተሰጠ ሲሆን፥ በቀሪ 43 የምርጫ ክልሎች ቅሬታዎች ላይ በቀጣይ ቀናት ውሳኔ እንደሚሰጥ ቦርዱ ገልጿል፡፡

Exit mobile version