አዲስ አበባ፣ ሰኔ 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) እንግሊዛዊው የፊት መስመር ተጫዋች ሃሪ ኬን በዓለም ዋንጫ ውድድር በርካታ ግቦችን በማስቆጠር የሀገሩን ልጅ ጋሪ ሊንከር ክብረ ወሰን ተጋርቷል፡፡
በአሜሪካ፣ ሜክሲኮ እና ካናዳ አዘጋጅነት እየተካሄደ በሚገኘው የ2026 የዓለም ዋንጫ የምድብ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ ትናንት ምሽት እንግሊዝ ክሮሺን 4 ለ 2 ማሸነፏ ይታወቃል፡፡
እንግሊዛዊው የ32 ዓመቱ ተጫዋች ሃሪ ኬን በጨዋታው 2 ግቦች ማስቆጠሩን ተከትሎ በዓለም ዋንጫ ውድድር ያስቆጠራቸውን የግብ መጠን 10 ማድረስ ችሏል፡፡
በዚህም ሃሪ ኬን ከእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን የቀድሞ ተጫዋች ጋሪ ሊንከር እኩል በዓለም ዋንጫ ውድድር ብቻ 10 ግቦችን በማስቆጠር ክብረ ወሰኑን ተጋርቷል፡፡
እንግሊዛዊው የቀድሞ ተጫዋች ጋሪ ሊንከር በ1986 እና 1990 የዓለም ዋንጫ ተሳትፎ ነው በመድረኩ ለብሔራዊ ቡድኑ 10 ግቦችን ያስቆጠረው፡፡
በዓለም ዋንጫ 10 ግቦችን በማስቆጠር ክብረ ወሰኑን የተጋራው ሃሪ ኬን 3ኛ የዓለም ዋንጫ ተሳትፎውን እያደረገ ይገኛል፡፡
ሃሪ ኬን በ2018 የዓለም ዋንጫ 6 ግቦችን በማስቆጠር በወቅቱ የመድረኩ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ በመሆን የወርቅ ጫማውን ማሸነፉ ይታወሳል፡፡
በ2022 የዓለም ዋንጫ ሁለት ግቦች እንዲሁም ትናንት ምሽት በ2026 የዓለም ዋንጫ በመጀመሪያ የምድብ ጨዋታ ሁለት ግቦችን አስቆጥሯል፡፡
በዚህም በዓለም ዋንጫ ያስቆጠራቸውን ግቦች 10 በማድረስ የሀገሩን ልጅ ክብረ ወሰን ተጋርቷል፡፡
ሃሪ ኬን በቀጣይ ጨዋታዎች ግብ የሚያስቆጥር ከሆነ ከጋሪ ሊንከር በመብለጥ በዓለም ዋንጫ ውድድር የምን ጊዜም የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ክብረ ወሰኑን የግሉ ያደርጋል፡፡
ሃሪ ኬን በአጠቃላይ ለብሔራዊ ቡድኑ 81 ግቦችን በማስቆጠርም የምን ጊዜም የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ተጫዋች ነው፡፡
በወንድማገኝ ጸጋዬ

