አዲስ አበባ፣ ሰኔ 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የ2018 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ሀገር አቀፍ ፈተናን ለማካሄድ ሰፊ የዝግጅት ሥራ ተከናውኗል አሉ የኦሮሚያ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች፡፡
የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ካሳሁን ገላና (ዶ/ር)÷ በክልሉ 180 ሺህ የሚሆኑ ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተናን እንደሚወስዱ ተናግረዋል፡፡
የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻልም በ1 ሺህ 406 ትምህርት ቤቶች ውስጥ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራቱን ነው የገለጹት፡፡
በዚህም ከመስከረም ወር ጀምሮ ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ባሉ የትምህርት አይነቶች ላይ የማጠናከሪያ ትምህርት ሲሰጥ መቆየቱን ጠቁመዋል።
ተማሪዎች የመለማመጃ ጥያቄዎችን በግልና በቡድን እንዲሰሩ መደረጉን ጠቅሰው÷ በተለይም ለሴት ተማሪዎች ልዩ ድጋፍ መሰጠቱን አስረድተዋል።
በክልሉ የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ሀገር አቀፍ ፈተና ሙሉ በሙሉ በበይነ መረብ ለመስጠት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት መሰራቱን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በተመሳሳይ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ሀገር አቀፍ ፈተና የሚወስዱ 7 ሺህ 679 ተማሪዎችን ውጤታማ ለማድረግ ሰፊ ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ተመስገን ዲሳሳ (ዶ/ር) ተናግረዋል።
ፈተናውን በስኬትና በታማኝነት ለመምራት የፈተና ማዕከላት ብዛት ቀድሞ ከነበረበት 2 ተነስቶ ወደ 18 ከፍ እንዲል መደረጉን አስረድተዋል፡፡
በተጨማሪም ከዘንድሮው የሀገር አቀፍ ፈተና ተፈታኞች መካከል 4 ሺህ 999 ወይም 65 በመቶ የሚሆኑት ፈተናውን በኦንላይን እንደሚወስዱ አመልክተዋል፡፡
ለዚሁ ተግባር የሚውሉ ታብሌቶች ተገዝተው ለፈተና ማዕከላቱ መሰራጨታቸውን ለፋና ዲጂታል አስረድተዋል።
የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ሀገር አቀፍ ፈተናን የሚወስዱ ተማሪዎች በቀሪ ቀናት አስፈላጊውን ዝግጅት እንዲያደርጉም ኃላፊዎቹ አሳስበዋል፡፡
የዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ከሰኔ 24 እስከ ሐምሌ 17 ቀን 2018 ዓ.ም የሚሰጥ ሲሆን÷ ለፈተናው በተፈጥሮ ሳይንስ 306 ሺህ 964 እና በማሕበራዊ ሳይንስ 257 ሺህ 255 በድምሩ 564 ሺህ 219 ተማሪዎች ተመዝግበዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተናውን በ97 ዩኒቨርሲቲዎች እና በ570 የክልል ማዕከላት ለመስጠት ዝግጅት መደረጉንም የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት አስታውቋል፡፡

