በለውጡ ዓመታት ዜጎችን ባስቀደመው ‘ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ’ አያሌ ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡
ከለውጡ በፊት በውጪ ሀገራት ለሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ጆሮ ሰጥቶ አለሁላችሁ የሚላቸው አልነበረም፡፡
ምን የውጭ ሀገራቱን ብቻ የሀገር ውስጡንም እናስታውሳችሁ፡፡
በአጋጣሚ መሪዎች በሚንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች የተገኘ ሰው፣ ወደ ኋላ ዙር ተብሎ ወደ መሪዎቹ እንዳያይ ይደረግ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡
ከለውጡ በኋላ መሪና ህዝብ አብሮ ይመክራል፤ ይሰራል፤ ሀገር ውስጥም ሆነ ከውጪ በአንድ መጓጓዣ ይሄዳል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይህንን አድርገዋል፡፡
ወደ ተለያዩ ሀገራት ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ባመሩባቸው ወቅት ችግር ውስጥ የነበሩ ኢትዮጵያውያን እና የትውልደ ኢትዮጵያውያንን ራሳቸው በሚጓዙበት አውሮፕላን ወደ ሀገርቤት ይዘው መጥተዋል፡፡
የኑሮ ሁኔታቸውን ፈትሸዋል፡፡
ባሉበት ሀገር የተሳካ ህይወት የሚመሩትን በማበረታታት፤ ችግር የገጠማቸው መፍትሄ ያገኙ ዘንድ እገዛ አድርገዋል።
እስር ቤት መግባትን ጨምሮ የከፋ የህይወት መስመር ውስጥ የሚገኙትን ደግሞ ለሀገራቸው እንዲበቁ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጓዙበት አውሮፕላን ይዘው በመመለስ መንግሥት ለዜጋ ያለውን ከፍተኛ ክብር በተግባር አሳይተዋል።
የለውጡ መንግሥት ዜጎች በህጋዊ መንገድ ወደ ውጪ ሀገራት ሄደው እንዲሰሩ በተለይም በመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት በተለያዩ የስራ መስኮች እንዲሰማሩ ከሀገራቱ መንግሥታት ጋር ህጋዊ ስምምነት በመፈጸም የስጋት ተጋላጭነታቸውን በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
በዚህም ዜጎች መብታቸው እና ደህንነታቸው ተጠብቆ እራሳቸውን እና ቤተሰባቸውን መርዳት እዲችሉ እየተደረገ ነው።
ባለፉት ዓመታት በመካከለኛው ምስራቅ በችግር ውስጥ የነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ወደ ሀገር እንዲገቡ ለማድረግ በርካታ ተቋማት የተቀናጀ እና የተናበበ ስራ ሰርተዋል።
በዚህም ዜጎች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ማድረግ ብቻ ሳይሆን በዘላቂነት ህይወታቸው መስመር እንዲይዝ የሚያስችል ድጋፍና ክትትል ተደርጎላቸዋል፤ እየተደረገላቸውም ይገኛል።

