አዲስ አበባ፣ ሰኔ 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አሜሪካ በቀድሞው የህወሓት ጽንፈኛ አመራሮች እና የቅርብ ቤተሰቦቻቸው ላይ የቪዛ እገዳ መጣሏን አስታወቀች፡፡
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ እንደገለጸው÷የቪዛ እገዳ የተጣለው የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት በመጣስ ተሳታፊ ናቸው በተባሉ አክራሪ የህወሓት አባላት እና የቅርብ ቤተሰቦቻቸው ላይ ነው፡፡
በዚህም የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በኢሚግሬሽንና ዜግነት ሕግ በተሰጣቸው ስልጣን በቀድሞ አክራሪ የህወሓት አመራሮችና የቅርብ ቤተሰቦቻቸው ላይ የቪዛ እገዳ መጣላቸው ተመላክቷል፡፡
የቪዛ እገዳው በትግራይ ክልል ያለውን ቀውስ ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት በማደናቀፍ ኃላፊነት ያለባቸው ወይም በዚህ ድርጊት ተባባሪ የሆኑ ግለሰቦችን ዒላማ ያደረገ ነው፡፡
አሜሪካ፣ በሰላምና በክብር መኖር ከሚሹ የትግራይ ሕዝብን ጨምሮ ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን መቆሟን እንደምትቀጥል መግለጫው አጽንኦት ሰጥቷል፡፡
አሜሪካ የቀድሞ ህወሓት ኃላፊዎችና በክልሉ ሰላምና መረጋጋት አደጋ የሚሆኑ ሌሎች ግለሰቦችን ለሕግ ተጠያቂ ለማድረግ የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ እንደምትቀጥልም አረጋግጣለች፡፡

