Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢትዮጵያ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ስደተኞች ጥበቃ እያደረገች ነው – አቶ አሕመድ ሽዴ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከ1 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች ጥበቃ እያደረገች ትገኛለች አሉ።
የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ስደተኞች በመጠለያ ጣቢያዎች ያላቸውን ሕይወት ከብሔራዊ ሥርዓቶች ጋር ማስተሳሰርን ማዕከል ያደረገውን የማካተት ፍኖተ ካርታ በይፋ አስጀምሯል።
በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ፣ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ባርሀም ሳሊህ፣ የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ጠይባ ሐሰን እና የክልል ርዕሳነ ተገኝተዋል።
አቶ አሕመድ ሽዴ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ አዲሱ ፍኖተ ካርታ በቀጣናው ያለው ግጭትና የአየር ንብረት መዛባት ያስከተለው የስደተኞች መፈናቀል ጫና ይቀንሳል።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከ1 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ጥበቃ እያደረገች እንደምትገኝ ተናግረዋል።
ይህን የምታደርገው ሰብዓዊ ኃላፊነት በመሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ለቀጣናዊ ሰላም፣ ህልውና እና መረጋጋት ስልታዊ አስተዋፅዖ ስላለው ጭምር መሆኑን አስረድተዋል።
ሚኒስትሩ የማካተት ፍኖተ ካርታው የኢትዮጵያን ስደተኞችን የመንከባከብ የረጅም ጊዜ ጉዞ ወደ ላቀ ምዕራፍ የሚያሸጋግር መሆኑን ማንሳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ፍኖተ ካርታው ከሀገራዊ ግቦች ጋር በቀጥታ ይተሳሰራል ያሉት ሚኒስትሩ÷ ዘላቂ ለውጥ ለማምጣት ፣እውነተኛ ዓለም አቀፍ የልማት ኃላፊነትን በጋራ መጋራት ወሳኝ እንደሆነ አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት፣ ከቀጣናዊ ድርጅቶች፣ ከልማት ተቋማት እና ከዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር ያላትን ትብብር አጠናክራ ለመቀጠል ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል።
የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ጠይባ ሀሰን በበኩላቸው የዛሬው ዕለት በኢትዮጵያ የስደተኞች ማካተት ጉዞ ውስጥ ትልቅ ምዕራፍ ነው፤ የተገቡ ቃሎችን ወደ ተግባር ለመቀየር ያለንን የጋራ ቁርጠኝነት የሚያንጸባርቅ ነውም ብለዋል።
Exit mobile version