አዲስ አበባ፣ ሰኔ 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አሜሪካ በቀድሞው የህወሓት ጽንፈኛ የቡድኑ አመራሮች እና የቅርብ ቤተሰቦቻቸው ላይ የጣለችው የቪዛ እገዳ የቡድኑን ጽንፈኝነትና አፍራሽ አካሄድ ለዓለም ማኅበረሰብ ያጋለጠ ነው አሉ የስምረት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ም/ቤት አባልና የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ ም/ሰብሳቢ አቶ ጠዓመ ዓረዶም።
አሜሪካ በቀድሞው የሕወሓት ጽንፈኛ አመራሮች እና የቅርብ ቤተሰቦቻቸው ላይ የቪዛ እገዳ መጣሏን አስታውቃለች፡፡
አቶ ጠዓመ ዓረዶም ውሳኔውን አስመልክተው እንደገለጹት÷ ርምጃው የአሜሪካ መንግሥት የቀድሞው ህወሓት ጽንፈኛ ቡድን በትግራይ ክልል ውስጥ እያደረገ ያለውን የጦርነት ትንኮሳና የሰላም ስምምነቱን የማፍረስ ሴራ በተገቢው መንገድ የተረዳ መሆኑን የሚያሳይ ነው።
አሜሪካ የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመበት ጊዜ ጀምሮ በቅርበት ስትከታተል እንደነበረችም ውሳኔው ማረጋገጫ ነው ብለዋል፡፡
ጽንፈኛው ቡድን የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ሙሉ በሙሉ በማፍረስ ጊዜው ያለፈበትንና የፈረሰውን ምክር ቤት በድጋሚ በማዋቀር የራሱን ፕሬዚዳንትና አዲስ ካቢኔ መምረጡ ለግጭትና ሁከት መዘጋጀቱን ያሳያል ነው ያሉት፡፡
በአሁኑ ወቅት ጽንፈኛ ቡድኑ ሰፊ ወታደራዊ ዝግጅት እና የጦርነት ትንኮሳዎችን እያደረገ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡
ስለሆነም አሜሪካ በዚህ ወቅት የወሰደችው ርምጃ ለሰላም ፈላጊዎች ትልቅ የምስራች መሆኑን ጠቁመው÷በትግራይ ሕዝብ ላይ የሰላም እጦትና ጦርነት የሚደግሰውን ቡድን ለይቶ የመታ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
አሁን የተወሰደው ርምጃ የሁሉም የትግራይ ሰላምና የለውጥ ፈላጊ ኃይሎችና የፓርቲያቸው ትግል ያመጣው ውጤት ነው፤ ሆኖም ግን ርምጃው ከዚህ በላይ ሊጠነክር እንደሚገባ አመልክተዋል።
ቡድኑ እስካሁን እያደረገ ያለው ተግባር ግልጽ የአሸባሪነት ስራ ነው ያሉት አቶ ጠዓመ÷ ልክ እንደ ሌሎች ዓለም አቀፍ አሸባሪዎች ሁሉ ይህ ቡድንም በአሜሪካ መንግሥትና በዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ዘንድ በልዩ ሁኔታ በአሸባሪነት ሊፈረጅ ይገባል ብለዋል፡፡
የቡድኑን አጥፊ እንቅስቃሴ የዓለም ማኅበረሰብ በሚገባ እንዲገነዘበው ፓርቲያቸው ትግሉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
የፌዴራል መንግሥትም ሕገ መንግስታዊ ኃላፊነቱን በመጠቀም የቀድሞው ሕወሓት ጽንፈኛ ቡድን ላይ ሕግ የማስከበር ሥራውን እንዲወጣ ጥሪአቅርበዋል።

