አዲስ አበባ፣ ሰኔ 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል የገጠር አካባቢዎችን ለማዘመን የተነደፈው “ሐሮሜ” ስትራቴጂ እየተተገበረ ነው አሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት ÷ የክልሉን ሕዝብ ኢኮኖሚያዊና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡
የገጠር አካባቢዎችን ለማዘመን የገጠር ሽግግር እውን ማድረግ ቀዳሚ ተግባር መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ለዚህም በአሁኑ ወቅት “ሐሮሜ” በተሰኘ ፕሮግራም ገጠርን የስደትና የልማት ዳርቻ ከመሆን አውጥቶ ወደ ዘመናዊ የልማት መሠረትነት እያሸጋገረው እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረገውን ፍልሰት፣ ሥራ አጥነትንና የልማት ክፍተት በመባባሱ፣ ለውጥ ለማምጣት በመጀመሪያ የገጠር ሽግግርን እውን ማድረግ የግድ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የ”ሐሮሜ” ፕሮግራም የሕንጻ ግንባታ ፕሮጀክት ብቻ ሳይሆን የልማት አስተሳሰብ ለውጥ መሆኑን ነው ርዕሰ መስተዳድሩ የገለጹት፡፡
ዓላማውም ገጠርን ከተማ ማስመስል ሳይሆን ዘመናዊነትን እስከ አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ደጃፍ ማድረስ ነው ብለዋል።

