Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኢትዮጵያን የምግብ ሥርዓት ለማዘመን የባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ጥረት ወሳኝ ነው

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ)ኢትዮጵያ በግብርና ስነ-ምህዳር ስትራቴጂ አማካኝነት የምግብ ስርዓቷን ለመለወጥ የጀመረችውን ጉዞ ለማሳካት፣ የባለድርሻ አካላትን የተቀናጀ ተሳትፎና የሀገር በቀል እውቀትን ከዘመናዊ ምርምር ጋር ማቀናጀት ወሳኝ መሆኑ ተመላከተ።

የኢትዮጵያ ዘላቂ የምግብ ስርዓትን ዘላቂ፣ ለጫናዎች የማይበገር እና ሁሉን አቀፍ ለማድረግ በሀገር አቀፉ የአግኢኮሎጂ ስትራቴጂ የተቀመጡ አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ የባለድርሻ አካላት መድረክ ተካሒዷል።በመድረኩ የመንግስት ተቋማት፣ የልማት አጋሮች፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ የምርምርና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ የግሉ ዘርፍ እና የወጣቶች ተወካዮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዘላቂ የምግብ ስርዓት እና የግብርና ስነ-ምህዳር ጥምረት ዋና ዳይሬክተር ባዩሽ ፀጋዬ (ዶ/ር) በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፤ ስትራቴጂው የኢትዮጵያን የምግብ ስርዓት በዘላቂና ለጫናዎች በማይበገር መንገድ ለመለወጥ የሚያስችል አጠቃላይ ማዕቀፍ ነው።

ዳይሬክተሯ፤ስትራቴጂው የግብርና ምርትን፣ አቀነባበርን፣ ስርጭትን እና ፍጆታን ከአካባቢ ጥበቃና ከጤና ጋር የሚያስተሳስር ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ ያለውን የረዥም ጊዜ የግብርና ስነ-ምህዳር ታሪክ፤ ማለትም የተቀናጀ የሰብልና እንስሳት እርባታ፣ የደንና እርሻ ቅንጅት እንዲሁም የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎችን በመሰረታዊነት እንደሚጠቀምም ተናግረዋል።

በዚህ ዓመት ይፋ የሆነው እና እስከ 2032 ዓ.ም የሚተገበረው ይህ ስትራቴጂ፤ ስድስት ዋና ዋና ግቦችን የያዘ ነው።

ዘላቂና ለጫናዎች የማይበገሩ አሰራሮችን ማስተዋወቅ፣ ምርምርንና ፈጠራን ማጠናከር፣ ሁሉን አቀፍ የገበያ ስርዓቶችን መፍጠር፣ ምቹ የፖሊሲ አየር መፍጠር፣ ማህበራዊ ተሳትፎን ማሳደግ እንዲሁም ዘላቂ የፍጆታ ልማዶችን መከተል ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ ምሁርና ተመራማሪ ዶክተር ፈለቀ ወልደየስ በበኩላቸው፤ የሀገር በቀል እውቀትን ከሳይንስ ጋር ማቀናጀት ለዘርፉ ፈታኝ ችግሮች ፈጠራ የታከለባቸው መፍትሄዎችን እንደሚያመጣ ገልጸዋል።

የአፈር ጤንነትን ለማሻሻል የተፈጥሮ ማዳበሪያዎችን መጠቀም፣ የሰብል ማፈራረቅ እና ብዝሃነትን መተግበር እንደሚገባ የጠቆሙት ምሁሩ፤ ከምርት በኋላ የሚደርስ ብክነትን ለመቀነስ የማከማቻና የገበያ ትስስርን ማጠናከር ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።

የግብርና ስነ-ምህዳር ከኮሜርሻል ግብርና ጋር የሚቃረን ሳይሆን ተመጋጋቢ መሆኑን በመድረኩ ላይ ተነስቷል።

የዘርፉን ውጤታማነት ለማረጋግጥ የተባይ መቆጣጠሪያን፣ የአፈር ጤንነትንና የተመጣጠነ ምግብን ያማከለ የግብርና አሰራርን በማስፋፋት ረገድ የሁሉም ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ጥረት እንደሚያስፈልግም አጽንኦት ሰጥተዋል።

የምክክር መድረኩ ስትራቴጂውን ወደ ተጨባጭ የልማት ውጤት ለመቀየር የሚያስችል የትብብርና ሎሌች እድሎችን በመዳሰስ ተጠናቅቋል።

Exit mobile version