Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ከንቲባ አዳነች የክረምት ወቅት የጽዳት ንቅናቄን አስጀመሩ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የ2018 ዓ.ም የክረምት ወቅት የጽዳት ንቅናቄ ሥራን አስጀምረዋል።

ከንቲባዋ በዚህ ወቅት እንዳሉት ፥ የጽዳት ሥራ ከራስ፣ ከቤት እና ከአካባቢ የሚጀመር የዕለት ተዕለት ተግባር ሊሆን ይገባል።

አዲስ አበባ በየጊዜው በአረንጓዴ እየለማችና እየጸዳች እንደምትገኝ ጠቁመው ፥ ይሁን እንጂ አሁንም ትኩረት የሚሹ አካባቢዎችና ሰፈሮች እንዳሉ ተናግረዋል።

ስለሆነም በደረጃው የሚገኙ አመራሮች፣ ሠራተኞች፣ ቤተሰቦችና ነዋሪዎች የጽዳት ሥራን በባለቤትነት ሊያከናውኑ ይገባል ነው ያሉት።

​የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓትን ለማዘመን ትልቅ ትኩረት ተሰጥቷል  ያሉት ከንቲባዋ ፥ ይህ የንቅናቄ አካሄድ አዲስ አበባን ይበልጥ ምቹና ጽዱ ከተማ ለማድረግ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

ደረቅ ቆሻሻ ሀብት በመሆኑ በአግባቡ በመለየት ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ማስወገድ  አስፈላጊ ነው ብለዋል።

በተለይም የክረምት ወራት የፍሳሽ መውረጃዎችና የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ ለበሽታ እንዳይዳርጉ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።

​ነዋሪዎች የንቅናቄው አምባሳደሮች በመሆን መዲናዋ ከማንኛውም ተላላፊ በሽታ የጸዳችና ጤናማ እንድትሆን የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።

በግዛቸው ግርማዬ

Exit mobile version