አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በትግራይ ክልል በቀድሞ አክራሪ የህወሓት ቡድን በተፈጠረው ሥርዓት አልበኝነት ምክንያት የዜጎች የደህንነት ስጋት እየጨመረ መጥቷል አሉ በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የመቐለ ከተማ የቀድሞ ከንቲባ አታክልቲ ኃ/ስላሴ።
አታክልቲ ኃ/ሥላሴ ከፋና ፖድካስት ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት ተጀምሮ የነበረው የታጣቂዎች ትጥቅ የመፍታት ሒደት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዳይደረግ የቀድሞ ህወሓት ቡድን እንቅፋት ሆኖ መቆየቱን ጠቁመዋል።
በዚህም ታጣቂዎች ወደ ሰላማዊ ሕይወት እንዳይመጡ ተግዳሮት በመሆን በጦርነት ውስጥ እንዲቆዩ የሚገፋፋ ሥራ ሲከውን መቆየቱን አብራርተዋል።
ቡድኑ በፕሪቶሪያው ስምምነት ሕዝቡ ያገኘውን የሰላም እና መረጋጋት ተስፋ በከፍተኛ ሥርዓት አልበኝነት እንዲተካ አድርጓል ነው ያሉት።
በክልሉ እንደ ት/ቤቶች እና ጤና ጣቢያዎች ያሉ መሠረታዊ የሕዝብ መገልገያ ተቋማት ከአገልግሎት ውጪ ሆነው የታጣቂዎች መሸሸጊያ እና መቀመጫ እንዲሆኑ ማድረጉን አስገንዝበዋል፡
የቀድሞ አህወሓት ጽንፈኛ አመራሮች ቡድን በሕዝብ ላይ በፈፀመው ወንጀል የሕግ ተጠያቂ ላለመሆን የፕሪቶሪያ ስምምነት እንዳይተገበር በማድረግ ሕዝቡ በሰላም ወጥቶ እንዳይገባ ስጋት ውስጥ መክተቱን ጠቁመዋል።
ክልሉ አስቀድሞ የኢኮኖሚ መዳከም የነበረበት ሲሆን ፥ በተፈጠረው ተጨማሪ ሰብዓዊ ቀውስ ማሕበረሰቡ ለከፋ ችግር መዳረጉን አመልክተዋል፡፡
ከፌዴራል መንግሥት እና ከተለያዩ ሰብዓዊ ተቋማት ለሕዝቡ የሚላኩ ሰብዓዊ ድጋፎች ለታለመላቸው ወገኖች ከመድረስ ይልቅ ፥ ለግልና ለተወሰኑ ቡድኖች ፍላጎት ማሟያ እየዋሉ መሆኑን አስረድተዋል።
ይህ ድርጊት በክልሉ የሚገኘውን ሕዝብ ለከፋ ችግር እየዳረገው መሆኑን ጠቅሰው÷ የሚመለከታቸው አካላት ችግሩ እንዲወገድ መሥራት እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።
በበጸሎት መንገሻ

