Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ጀርመን ከኮትዲቯር…

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በዓለም ዋንጫ የምድብ ሁለተኛ ጨዋታ መርሐ ግብር ጀርመን ከኮትዲቯር የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል፡፡
ጨዋታው በካናዳ ቶሮንቶ ስታዲየም ምሽት 5 ሰዓት ላይ የሚካሄድ ሲሆን ÷ አሸናፊው ቡድን ጥሎ ማለፉን መቀላቀሉን ያረጋግጣል፡፡
በመጀመሪያው የምድብ ጨዋታ ጀርመን ኩራሳኦን 7 ለ 1 እንዲሁም ኮትዲቯር ኢኳዶርን 1 ለ 0 ማሸነፋቸው ይታወሳል፡፡
በሌላ ጨዋታ ምሽት 2 ሰዓት ላይ በሂውስተን ስታዲየም ኔዘርላንድስ ከስዊዲን የሚያደርጉት ጨዋታ በጉጉት ይጠበቃል፡፡
ስዊዲን በመጀመሪያው የምድብ ጨዋታ ቱኒዚያን ማሸነፏን ተከትሎ የዛሬውን መርሐ ግብር በድል መወጣት ከቻለች ጥሎ ማለፉን የምትቀላቀል ይሆናል፡፡
በመጀመሪያ የምድብ ጨዋታዋ ከጃፓን 2 አቻ የተለያየችው ኔዘርላንድስ በበኩሏ በውድድሩ ለመቆየት የዛሬውን ጨዋታ ማሸነፍ ይጠበቅባታል፡፡
ትናንት ምሽት በተደረጉ ጨዋታዎች ቱርክዬ በፓራጓይ 1 ለ 0 መሸነፏን ተከትሎ ከዓለም ዋንጫው ተሰናብታለች፡፡
ሲያትል ላይ አውስትራሊያን የገጠመችው አሜሪካ 2 ለ 0 ያሸነፈች ሲሆን ÷ በዚህም ሜክሲኮን ተከትላ ጥሎ ማለፉን የተቀላቀለች ሌላኛዋ አዘጋጅ ሀገር ሆናለች፡፡
በሌሎች ጨዋታዎች ሄይቲን የገጠመችው ብራዚል ማቲያስ ኩኛ (ሁለት) እንዲሁም ቪኒሺየስ ጁኒየር ባስቆጠሯቸው ግቦች 3 ለ 0 አሸንፋለች።
ሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር ሞሮኮ ደግሞ በእስማኤል ሳይባሪ ብቸኛ ግብ ስኮትላንድን 1 ለ 0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችላለች፡፡
በአቤል ነዋይ
Exit mobile version