Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በአማራ ክልል በተምች የተወረረ 51 ሔክታር መሬት ነጻ ተደረገ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 24፣2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል በመጤ ተምች ተወሮ ከነበረው የበቆሎና ማሽላ ሰብል ከተዘራ ማሳ ውስጥ 51 ሺህ ሄክታሩ ኬሚካል በመርጨትና በባህላዊ ዘዴ መከላከል መቻሉን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው የሰብል ጥበቃ ባለሙያ አቶ አሻግሬ እንዳየን የአሜሪካ መጤ ተምች ካለፈው ሰኔ አጋማሽ ጀምሮ በ57 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ በለማ የበቆሎና ማሽላ ሰብል ተከስቶ መቆየቱን አስታውሰዋል።
የተከሰተውን አውዳሚ ተምችም የሰው ጉልበትን በመጠቀም በባህላዊ መንገድ እና ኬሚካል በመርጨት በሰብል ላይ ጉዳት ሳይደርስ ማስወገድ መቻሉን ተናግረዋል።
በመከላከል ስራው ከ16 ሺህ ሊትር በላይ ፀረ-ተባይ ኬሚካል ጥቅም ላይ ሲውል ከ114 ሺህ የሚበልጡ አርሶ አደሮችና የግብርና ባለሙያዎች መሳተፋቸውንም ገልፀዋል።
በቀሪ ስድስት ሺህ ሄክታር መሬት የሚገኘውን የአሜሪካ መጤ ተምች በሰብል ላይ የከፋ ጉዳት ከማድረሱ በፊት የማስወገድ ስራም በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝም መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

Exit mobile version